የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ፎረም የ2010 ትምህርት ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ዩኒቨርሲቲ አቀፍ ውይይት ጥር 09/2010 ዓ/ም ተካሂዷል፡፡ ከዚህ ቀደም በየካምፓሶቹ በተከናወኑ የትምህርት ጥራትና የመልካም አስተዳደር ፎረም ውይይቶች በተማሪ መኝታ፣ ምግብ፣ ክሊኒክ፣ ቤተ-መጽሐፍት፣ ቤተ-ሙከራና ሬጂስትራር አገልግሎቶች፣ በመማር ማስተማር፣ በትምህርት ልማት ሰራዊት ትግበራ፣ በፀጥታና ደህንነት እንዲሁም በተማሪ፣ መምህራንና የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ሥነ-ምግባር ዙሪያ የተነሱ ችግሮች ጥቅል ሪፖርት ቀርቦ ተጨማሪ አስተያየትና ጥያቄዎች፣ ምላሾችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የቤተ-መጽሐፍት መጨናነቅ፣ የመጸዳጃ ቤት ችግር፣ የሻወር ውሃ መቆራረጥ፣ የልብስ ማጠቢያ ቦታ ችግር፣ አምሽተው የሚመጡ ተማሪዎች የዲሲፕሊን ጥሰት፣ ስርቆት፣ የኩረጃ መስፋፋት፣ የውጭ ሀገር መምህራን በተለይ በትምህርት አቀራረባቸው ከተማሪው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አለመጣጣም፣ የመጽሐፍት እጥረት፣ የ1ለ5 አደረጃጀት በቂ የመወያያ ስፍራ አለመኖር እንዲሁም የጥበቃ ሠራተኞች ተማሪዎችን በአግባቡ አለማስተናገድ ከተነሱ ችግሮች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት ምላሽ ከተነሱ ችግሮች መካከል ጥቂቶቹ የተፈቱ መሆናቸውን ጠቅሰው በሂደት ላይ ያሉትን ከፍፃሜ ለማድረስና እና ቀሪዎቹን በአጭርና በረዥም ጊዜ ዕቅዶች መፍትሔ ለማበጀት በትጋት የሚሠሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ውይይቱ በየት/ት ክፍሉና በየኮሌጅ ደረጃ ሲካሄድ መቆየቱን አውስተው በአንደኛው ሴሚስቴር ማጠናቀቂያ በዩኒቨርሲቲ አቀፍ ደረጃ መካሄዱ በሁለተኛው ወሰነ ትምህርት በችግሮቹ ላይ የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ጥሩ ግብዓት መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ ‹‹የትምህርት ጥራት›› እና ‹‹መልካም አስተዳደር›› ሁለት ግዙፍ ጉዳዮች መሆናቸውን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ በርዕሰ ጉዳዮቹ ላይ በየትምህርት ክፍሉ ወቅታዊ ውይይት በማድረግ ያለፉ አፈፃፀሞችን መገምገም እና በየደረጃው ተገቢ ማስተካከያዎችን እያስቀመጡ መሄድ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡