የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ለህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የአስተዳደር ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች በሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዙሪያ ጥር 2/2010 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡

በስልጠናው ፆታና ሥርዓተ-ፆታ፣ የሥርዓተ-ፆታ ሚናዎች፣ የሥርዓተ-ፆታ ክፍፍል፣ የሥርዓተ-ፆታ ፍላጎቶች፣ የሥርዓተ-ፆታ ሚዛናዊነት፣  የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት፣ የሥርዓተ-ፆታ ልማት፣ ፆታዊ ጥቃትና የመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተካተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በሥርዓተ-ፆታ ጉዳይ ዙሪያ ሰዎች ያላቸው ግንዛቤ የተዛባ በመሆኑ የተሳሳተ አመለካከትን በመቅረፍ በሀገሪቱ ልማት የሁለቱም ፆታዎች ተሳትፎና ተጠቃሚነት መመጣጠን እንዳለበት ግንዛቤ ለመፍጠር ስልጠናው መዘጋጀቱን የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለሙያ አቶ መሰለ መርጊያ ገልፀዋል፡፡ የሴቶችን ተሳትፎ ከወንዶች ጋር ለማመጣጠን ድጋፍ ማድረግ ተገቢ በመሆኑ በትምህርት፣ በቅጥር፣ በኃላፊነት ቦታዎችና በኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ተሳትፏቸው እንዲያድግ እየተሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ታምሩ ሽብሩ በበኩላቸው ሠራተኞቹ በሚያገኙት የሥርዓተ ፆታ ግንዛቤ የራሳቸውን፣ የካምፓሱን፣ የዩኒቨርሲቲውን ብሎም የውጪውን ማህበረሰብ ከፆታዊ ጥቃቶች፣ መሰል አሉታዊ ድርጊቶች እና የህግ ጥሰቶች መከላከል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡