የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ህብረት የፓርላማ ምርጫ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት፣ የተማሪዎች አገልግሎት ማዕከል ዳይሬክተር፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ከ5ቱም ኮሌጆች የተወጣጡ ምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ታዛቢዎች እና መምህራን በተገኙበት ጥር 5/2010ዓ.ም በሰላማዊ መንገድ ተካሂዷል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ተማሪ ደምሰው ፈረደ የተማሪ ህብረት ፕሬዝደንት ሆኖ ሲመረጥ ተማሪ አዳነ ወርቄ ከጫሞ ካምፓስ፣  ተማሪ የሺወርቅ ደለለኝ ከአባያ ካምፓስ፣ ተማሪ ዘገየ ታደሰ ከኩልፎ ካምፓስ እና ተማሪ ኤርምያስ ዓለምሸት ከነጭ ሳር ካምፓስ የህብረቱ ምክትል ፕሬዝደንቶች ሆነው ከየካምፓሱ ተመርጠዋል፡፡

ህብረቱ በ2009 የትምህርት ዘመን በስራ አስፈፃሚ መማክርት፣ ክበባት፣ ማህበራት እና ኮሚቴዎች የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኑን የቀድሞው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝደንት መምህር ጌታቸው ወርቁ ተናግሯል፡፡ ከዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎቹ ባሻገር ህብረቱ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ወቅታዊ ያለመረጋጋትን ለመቅረፍ እና በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተማሪዎችን በሚመለከቱ አስተዳደራዊ ሥራዎች፣ አገልግሎቶች፣ የመዝናኛና የዲሲፕሊን ጉዳዮች በመሳተፍ ጉልህ ሚና መጫወቱንም ገልጿል፡፡

በሀገር አቀፍ ልዩ የማህበረሰብ ስልጠና ተማሪዎችን በማስተባበር፣ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን በመቀበል እንዲሁም የሁሉም ዲፓርትመንት ክበባት የአካዳሚክ ተጠሪ ተማሪዎችን በቅርበት በማግኘት የትምህርት አሰጣጥ ሂደቱን በመከታተል ረገድ ህብረቱ ጠንካራ ሥራ ማከናወኑን መምህር ጌታቸው ተናግሯል፡፡

የተማሪዎችን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመደራጀት መብት በማስጠበቅ፣ የወንድማማችነትና የእህትማማችነት  ግንኙነትን በማጠንከር  እንዲሁም በዘር፣ በሐይማኖትና በፖለቲካ አቋም ልዩነት ሳይደረግ ምርጫው መፈፀሙን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ የህብረቱ ተመራጮች የመማር ማስተማር ሂደቱን ሰላማዊ ለማድረግና የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ተወጥተው በሚሰጡት አገልግሎት እርካታ ለማግኘት የበኩላቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡ ሁሉን በእኩልነት በማገልገል ለአካባቢውና ለሀገር ጥሩ አርዓያ መሆን ያስፈልጋል ያሉት ፕሬዝደንቱ ለተማሪዎች በሚያደርጉት ማንኛውም በጎ ሥራ ዩኒቨርሲቲው ከጎናቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡