የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት በአባያና ጫሞ ሐይቆች ተፋሰስ ሊከናወኑ በሚገባቸው የተፈጥሮ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ጥር 25/2010 ዓ/ም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ምክክር አድርጓል፡፡

የምክክሩ አስፈላጊነት ምሁራንና ባለድርሻ አካላት በሐይቆቹ ዙሪያ የሚያካፍሉትን እውቀትና ጥናታዊ ግኝቶች በማዳበር ሐይቆቹን ለመታደግ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ መሆኑን የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ገልፀዋል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የነጭ ሣር ብሄራዊ ፓርክን የቆዳ ስፋት 50 በመቶ የሚሸፍኑትን ሐይቆች ከተጋረጡባቸው ፈተናዎች ለመታደግ ብሎም ቀድሞ ወደ ነበሩበት ለመመለስ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸውን ምርምሮች ወደ ተግባር እንዲቀይር ባለድርሻ አካላት አጋርነታቸውን በተግባር ሊያሳዩ ይገባል ብለዋል፡፡

የVLIR-IUC ፕሮጀክት ማኔጀርና የዘርፉ ተመራማሪ ዶ/ር ፋሲል እሸቱ በምክክር መድረኩ እንደተናገሩት የደኖች መጨፍጨፍ፣ በሐይቆቹ አቅራቢያ ልቅ የግብርና ሥራ መስፋፋት፣ በሐይቆቹ ላይ የሚጠኑ ጥናቶች ወደ ተግባር ያለመቀየር፣ የሐገሪቱን የሐይቅና የመሬት አጠቃቀም መመሪያዎችና የህግ ማዕቀፎች በአግባቡ ያለመተግበር እና የሚመለከታቸው አመራር አካላት ሐይቆቹን ለመታደግ ያላቸው ቁርጠኝነት ደካማ መሆን ሐይቆቹ ከተጋረጡባቸው ችግሮች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የአባያና ጫሞ ሐይቆችን መታደግ የህዝቦችን ህይወት መታደግ ነው ያሉት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ ከሐይቆቹ ጋር በተያያዘ በርካታ ጥናቶች ቢኖሩም ተቀናጅቶ ካለመስራትና የሀገሪቱ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በትክክል ካለመተግበሩ ጋር ተያይዞ ጥናቶቹን ወደ ተግባር መቀየር እንዳልተቻለ ገልፀዋል፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ሁሉም ባለድርሻ አካላት የሐይቆቹን ጉዳይ የህልውና ጉዳይ አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ዶ/ር የቻለ ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ለሐይቆቹ ደህንነት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት፣ የፖለቲካ አመራር አካላትን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ ያሳተፉ ውይይቶች ማካሄድ እና በሐይቆቹ ገባር ወንዞች አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠት ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው ብለዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ከነጭ ሣር ብሄራዊ ፓርክ፣ ከGIZ ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ ከዞንና ከወረዳ ግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ መምሪያና ጽ/ቤት የተወጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡