ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ ጎፋ ዞን 17 ወረዳዎች ለተወጣጡ 20 የስፖርት ባለሙያዎች ከጥር 05 ጀምሮ ለተከታታይ 10 ቀናት በገበጣ፣ ትግል፣ ቀስት፣ ፈረስ ጉግስና መሰል 11 ባህላዊ ስፖርቶች የመጀመሪያ ደረጃ የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥቷል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው የስፖርት አካዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ቾምቤ አናጋው ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ቀደም በተለይ በዳኝነትና በአሰልጣኝነት ብቁ የስፖርት ባለሙያዎችን ለማፍራት ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን አስታውሰው ስልጠናው የባህል ስፖርት አሰልጣኞችን በበቂ ሁኔታ ለማፍራትና የባህል ስፖርተኞችን ተሳትፎ በዞንና በወረዳ ደረጃ ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ  አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባህላዊ ስፖርቶች ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ህይወት መሀመድ እንደገለፁት እነዚህ ባህላዊ ስፖርቶች በኢትዮጵያ  ከ3000 ዓመታት በፊት ሲዘወተሩ የነበሩ ሲሆን ነገር ግን  ቀስ  በቀስ እየጠፉ  ሄደዋል፡፡ ይህን በመገንዘብ የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር በተወሰኑ የባህል ስፖርቶች የአሰልጣኞችን ቁጥር በማሳደግ የባህል ስፖርትን ለማስፋፋት ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡ በመሆኑም ስፖርቱን ለማጠናከር ባለሙያዎቹ በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር በ11 ባህላዊ የስፖርት ዓይነቶች ስልጠና መስጠታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የስፖርት ባለሙያዎች በተጨማሪ ስልጠና ታግዘው ባህላዊ ስፖርቶቹን እንዲያስፋፉና በሀገር አቀፍ ደረጃ ተሳታፊ የሚሆኑ ስፖርተኞች እንዲወጡ ትኩረት አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመስጠቱ ሊበረታታ እንደሚገባም ባለሙያዋ ገልጸዋል፤ አተገባበሩን በዘላቂነት መከታተል እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ሰልጣኝ ህይወት በቀለ ስልጠናው በተግባር የተደገፈ በመሆኑ ማወቅ የሚገባኝን ነገር አሳውቆኛል፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ ብሏል፡፡ ስልጠናውን የሰጡ ባለሙያዎች በተለያዩ ቦታዎች የባህል ስፖርት ፕሮጀክት አቋቁመው እነዚህን ስፖርቶች በዘላቂነት ሊያጠናክሩ እንደሚገባም አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

በስልጠናው የተሳተፉ የስፖርት ባለሙያዎች የመጀመሪያ ደረጃ የአሰልጣኝነት የእውቅና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡