የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት የካቲት 5/2010 ዓ/ም ተፈራርሟል፡፡

በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የሚገኙትን ከ80 ሚሊየን በላይ በፓተንት የተመዘገቡ ሰነዶች ለዕውቀት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለሀገር እድገት ግንባታ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ጽ/ቤቱ ከሚመለከታቸው ባለ ድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መሥራት ያለበት መሆኑን በመገንዘብ እና ዩኒቨርሲቲውም ስለ ፓተንት ህግ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግና በፓተንት የተመዘገቡ ፈጠራዎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችሉ አሠራሮችን ለመፍጠርና ለማጎልበት በማሰብ የውል ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱ በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት የሚገኙ በፓተንት ራይት የተመዘገቡ ፈጠራዎችን ዩኒቨርሲቲው እንደፍላጎቱ በመምረጥና በማደራጀት የፈጠራዎቹን ምንነት፣ ጥቅምና አጠቃቀም በተመለከተ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች እንዲሰጡና መረጃዎቹ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውሉ ለማድረግ ያስችላል፡፡ ይህም በዋናነት በእውቅና ብቻ የከሰሙ የፈጠራ ሥራዎች ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት አበርክቶ እንዲያደርጉ ከማገዝ አንፃር ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ያግዛል፡፡

በዚሁ መሰረት ስምምነቱን የተፈራረሙት ተቋማት ስለ ፓተንት መረጃ ባለሙያዎቻቸው ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የማከናወን፣ የተመረጡ የፓተንት መረጃዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል አቅማቸው በሚፈቅደው መጠን ያላቸውን የገንዘብ፣ የእውቀትና የማቴሪያል ሀብት የማቀናጀት፣ ዓለም አቀፍ መረጃዎችን ለማግኘት በዚህ ስምምነት መሰረት የዌብ ሳይቶችን የይለፍ ቃል (password) የማግኘትና ጥቅም ላይ የማዋል መብት ይኖራቸዋል፡፡ ተቋማቱ ዘላቂና ተከታታይ የመረጃ ልውውጥ ሥርዓትና የምክክር መድረኮችን በማዘጋጀት ሥራውን የሚከታተሉና የሚያስተባብሩ ተወካዮችን ይመድባሉ ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ገልጸዋል፡፡