የሳውላ ካምፓስ የማህበረሰብ አገልግሎት ማስ/ጽ/ቤት በሳውላ ከተማ ለሚገኙ 11 የመንግስት መሥሪያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ከየካቲት 14-16/2010 ዓ/ም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተግባቦት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

ስልጠናው የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ዓለም አቀፍ መግባቢያ የሆነውን እንግሊዝኛ ቋንቋ ተጠቅመው በመማር ማስተማርና በተለያዩ ጉዳዮች ወደ ከተማዋ ከሚገቡ የውጭ ሀገር ዜጎች ጋር መግባባት እንዲችሉና ፈጣን ምላሽ እንዲሰጡ ታልሞ የተዘጋጀ መሆኑን የካምፓሱ እንግሊዝኛ መምህርና የስልጠናው አስተባባሪ መ/ር ተስፋዬ ፈረደ ገልፀዋል፡፡

ሰልጠኞቹ ቋንቋውን በቀላሉ እንዲረዱ የስልጠና ሞጁል ተዘጋጅቶ የተሰጣቸው ሲሆን ቋንቋውን በይበልጥ ማዳበር እንዲችሉ በቡድን ተደራጅተው ልምምድ የሚያደርጉበት ሁኔታ ተመቻችቷል፡፡

እንደ አስተባባሪው ገለፃ ስልጠናው ከዚህ ቀደም ለካምፓሱ የአስተዳደር ሠራተኞች መሰጠቱን አውስተው ነገር ግን ከካምፓሱ አስተዳደር ውጭ ላሉ የመንግስት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ሲሰጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ በቀጣይም ዕድሉን ላላገኙ የከተማዋ የሥራ ኃላፊዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች ለመስጠት ዕቅድ ተይዟል፡፡

የሳውላ ከተማ ንግድ ኢንደስትሪና ትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ያዕቆብ ደበላ በአስተያየታቸው በከተማው ሰፋፊ የልማት ሥራዎችና የዩኒቨርሲቲውን መሰረተ-ልማት ግንባታዎች ለማከናወን የውጭ የሥራ ተቋራጮች በሚፈለጉበት ጊዜ እንዲሁም የውጭ ሀገር እንግዶችና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮችን ተቀብሎ ለማስተናገድ እንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎትን ማጎልበት አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ የስልጠና ዕድሉን በማግኘታቸው መደሰታቸውንም ገልፀዋል፡፡

የሳውላ ከተማ ሴቶችና ህጻናት ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ያፖ በበኩላቸው ስልጠናው በአጭር ቀናት ውስጥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክህሎቴን ለማዳበር ቀለል ያሉ የመግባቢያ ስልቶችን ስላሳወቀኝ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡