የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕ/ጽ/ቤት ከሳውላ ካምፓስ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በምርምር ንድፈ ሀሳብ አጻጻፍና አዘገጃጀት፣ በታዋቂ ጆርናሎች ላይ የሚታተሙ የምርምር አርቲክሎች አጻጻፍና ይዘት፣ በዘርፈ-ብዙ ማህበረሰብ አቀፍ ትላልቅ ፕሮጀክቶች (Grand projects) አዘገጃጀት፣ ለምርምር ሥራ በሚውሉ የተለያዩ ሶፍትዌሮች (STATA,GIS, and SPSS) አጠቃቀም፣ አተረጓጎም እና ትንታኔ ላይ ከየካቲት 16-20/2010 ዓ.ም ለ5 ተከታታይ ቀናት ለ25 የሳውላ ካምፓስ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የመጀመሪያ ዙር የአሰልጣኞች ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

እየተሠሩ ያሉ ምርምሮች በእውቀት ላይ የተመሰረቱና የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ እንዲሆኑ፣ ሰልጣኞች ሣይንሳዊ የትንተና ዘዴዎችን እንዲጠቀሙ ለማስቻልና በዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ እንዲመዘገቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እንዲሁም የካምፓሱ መምህራን በአብዛኛው አዲስ በመሆናቸው በምርምር ዘርፍ ያለውን የእውቀት ክፍተት ለማጥበብ ታልሞ ስልጠናው መዘጋጀቱን የምርምር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተሾመ ይርጉ ገልፀዋል፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደተናገሩት አንድ አጥኚ ምርምር ማድረግ ሲፈልግ በዋናነት የቤዚክ ሪሰርች(Basic research)፣ የአክሽን ሪሰርች (Action research) እና የፕሮጀክት ሪሰርች (project research) ምንነትንና አተገባበርን እንዲሁም የኳሊቴቲቭ(qualitative) እና ኳንቲቴቲቭ (quantitative) የምርምር ጽንሰ ሀሳቦችን ማወቅ ይገባዋል፡፡ ከካምፓሱና ከመምህራኑ አዲስ መሆን ጋር ተያይዞ ከዚህ ቀደም በካምፓሱ ብዙ ምርምሮች ያልተከናወኑ ሲሆን ይህ ስልጠና በቂ ክህሎትና ግንዛቤ አስጨብጦ በምርምር ዘርፍ ስኬታማ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡

የካምፓሱ ዲን አቶ ገ/መድህን ጫሜኖ ዩኒቨርሲቲዎች ምርምርን መሠረት ያደረጉ የማስተማሪያ ተቋማት እንደመሆናቸው የካምፓሳችን መምህራን ይህን ስልጠና ማግኘታቸው በምርምሩ ዘርፍ የበለጠ እንዲሠሩ ያግዛቸዋል ብለዋል፡፡

ሰልጣኝ መ/ር ተስፋዬ ፈረደና መ/ር ዘለቀ ዶሳ ስልጠናዉ በአስፈላጊ ጊዜ በመሰጠቱ መደሰታቸዉን ገልጸዉ በቀጣይም ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን በምርምር ሥራ ተሳታፊ በመሆን የህብረተሰቡን ችግር ለመፍታትና የዩኒቨርሲቲውን መልካም ገጽታ ለመገንባት የተቻለንን ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡