የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ጀርመን እና ስዊዘርላንድ ከሚገኙ የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት አጋር ተቋማት ጋር በመተባበር በተሻሻሉ የታዳሽ ኃይል ሞዴሎች አተካከልና አጠጋገን ላይ ከየካቲት 26 - መጋቢት 7/2010 ዓ/ም የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

በዩኒቨርሲቲው የታዳሽ ኃይል ምርምር ማዕከል ኃላፊ አቶ ዘላለም ግርማ እንደገለፁት በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የሚሠሩ ባለሙያዎችን አቅምና ቁጥር በበቂ ሁኔታ ማጎልበት ዘርፉን ከማሳደግ ባለፈ ለአገር ልማትና ለማህበረሰቡ ዘርፈ ብዙ ተጠቃሚነት አስተዋጽኦው የጎላ ነው፡፡ ስለሆነም ስልጠናው ለዘርፉ ባለሙያዎች የታዳሽ ኃይል ሞዴሎች ተከላና ጥገና ላይ የንድፈ ሀሳብና የተግባር እውቀትና ክህሎት በማስጨበጥ በቂ የሰው ኃይል ለመፍጠር ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ ይህም በፕሮጀክቱ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን ለማስቀጠልና በቀጣይ ከፀሐይ ብርሃን በሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ሊሠሩ የሚችሉ የውሃ ፓምፖችና ሌሎች ሥራዎች ላይ ተጨማሪ ግንዛቤና አቅም  ለመፍጠር ይረዳል፡፡

በኤሌክትሪካል ምህንድስና ት/ክፍል ቤተ-ሙከራ ለሦስተኛ ዙር በተሰጠው ስልጠና ከዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂና የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች እና ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ተቋማት የተወጣጡ ከ30 በላይ የኢነርጂ ዘርፍ ባለሙያዎችና መምህራን ተሳትፈዋል፡፡

የሳሃይ ሶላር ታዳሽ ኃይል ፕሮጀክት በጋሞ ጎፋ ዞን በሚገኙ የገጠር ቀበሌያት የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን የመብራት ተጠቃሚ ለማድረግ በ2001 ዓ/ም ተጀምሯል፡፡ ፕሮጀክቱ በድጋሚ ከሚያዝያ/2007 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ዓመታት አገልግሎቶችን በማሻሻል በተለይም በዞኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው የገጠር ቀበሌያት በሚገኙ የጤና ማዕከላት አገልግሎቱን በማዳረስ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማስፋት በማለም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

የመንግስት ትኩረት በሆነው የእናቶችና ህፃናት ጤና እንደተቋም አስተዋጽኦ ለማድረግ በዞኑ የገጠር ቀበሌያት ተጠቃሚነትን ለማስፋት ፕሮጀክቱ በ50 የጤና ተቋማት የፀሐይ ኃይል ተከላና ጥገና በማከናወን የታዳሽ ኃይል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በመሥራት ላይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በ23 ጤና አጠባበቅ ማዕከላት ተከላው ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ማዕከሉ ገልጿል፡፡