የዩኒቨርሲቲው የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ከጋሞ ጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ሰገን አካባቢ ህዝቦች፣ ወላይታ እና ዳውሮ ዞኖች ለተመለመሉ 146 ዕጩ ሴት ርዕሳነ መምህራን ከየካቲት 16/2010 ዓ/ም ጀምሮ ለተከታታይ ሦስት ወራት የአመራርነት ክህሎት ስልጠና በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡ ምልመላው በየዞኖቹ በትምህርት ዝግጅት፣ በሥራ ልምድ፣ በሥራ አፈፃፀምና ሥነ-ምግባር በማወዳደር ተከናውኗል፡፡

የአመራርነት ክህሎትና ብቃትን በማጎልበት በ1ኛ ደረጃ ት/ቤቶች የሴት አመራርነት ድርሻን ወደ 50 በመቶ ማሳደግና የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በመጠቀም ፕሮግራሙን ወደ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ማሸጋገር የስልጠናው ዋነኛ ዓላማ እንደሆነ የስልጠናው አስተባባሪ መ/ር ሰለሞን ሳጶ ገልፀዋል፡፡ አመራርነት የት/ቤቱን ወይም የተቋሙን ዕቅድ ለማሳካት የተቀመጡ ግብዓቶችን ያለምንም ብክነት በተገቢው ቦታ ላይ ተጠቅሞ ከግብ ማድረስ እንዲሁም  የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የመደገፍ ሂደት መሆኑን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡

ስልጠናው 70 በመቶ በተግባር ልምምድና 30 በመቶ በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ የሚሰጥ ሲሆን በአመራርነት ሙያ ምንነትና አተገባበር፣ በትምህርት ፖሊሲና በዘርፈ-ብዙ የትምህርት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ ሰልጣኞች የፓናል ውይይት፣ የፕሮጀክት ሥራዎች ቀረፃና በንድፈ-ሃሣብ የሰለጠኑት በት/ቤት ተግባራዊ መሆኑን ለማረጋገጥ የትምህርት ቤቶች ጉብኝት ያደርጋሉ፡፡

የሥነ-ትምህርትና ሥነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት ዲን ዶ/ር ኢዮብ አየነው ሁሉም ሰልጣኞች ከስልጠናው በኋላ በርዕሰ መምህርነት የሚመደቡ በመሆናቸው በዕውቀትና በክህሎት ብቁ ሆነው የሚጣልባቸውን ኃላፊነት በተግባር በማሳየት ለሌሎችም ጥሩ አርአያ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በአመራርነት ሙያ ላይ የበቁ ሴት አመራሮችን ከማፍራት አንፃር ጉልህ   አስተዋፅኦ እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ወደ አመራርነት ከመግባታቸው በፊት መሰጠቱ በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸውን ጉዳዮች እንዲለዩና በቂ ግንዛቤ ጨብጠው በሙያው ስኬታማ እንዲሆኑ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡