የዩኒቨርሲቲው የህግ ተማሪዎች ማህበር ከ1ኛ- 4ኛ ዓመት ላሉ 35 የህግ ተማሪዎች የ1 ለ 5 ቡድን ተጠሪዎች በተማሪዎች የሥነ-ምግባር መመሪያ ላይ መጋቢት 10/2010 ዓ/ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የስልጠናው ዓላማ የህግ ተማሪዎች ህጉን ካለማወቅ የተነሳ ከሚደርሱባቸው የተለያዩ የሥነ-ምግባር ችግሮች መታደግ እንዲሁም የግቢውን ሰላምና ፀጥታ ከማስጠበቅ አንፃር ለሌሎች ተማሪዎች ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና እንዲኖራቸው ማስቻል እንደሆነ የህግ ተማሪ የሆነው የማህበሩ ሰብሳቢ ተማሪ  እምሻው ተሾመ ተናግሯል፡፡

እንደ ተማሪ እምሻው ገለፃ ህግን አለማወቅ ከተጠያቂነት ስለማያድን ሁሉም ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለውን ደንብና መመሪያ ብሎም መብትና ግዴታዎችን ጠንቅቀው ማወቅና መተግበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተጨማሪም የህግ ተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን ለህግ ተከባሪነትና ተፈፃሚነት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡

የህግ ትምህርት ቤት መምህርና የፕሮግራሙ አስተባባሪ አቶ ክብሮም መክብብ እንደተናገሩት ስልጠናው የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አንፃር የሥነ-ምግባር ህግ ወሳኝነት ስላለው ተማሪዎችም ከሥነ-ምግባር ጥሰት ራሳቸውን እንዲጠብቁና ሌላውንም እንዲከላከሉ ያሳውቃል፡፡

የማህበሩ የህዝብ ግንኙነት ተጠሪ ተማሪ ሰለሞን ወዳጁ የሥነ-ምግባር ጥሰቶችና የሚያስከትሉትን ቅጣቶች አስመልክቶ ባቀረበው ማብራሪያ መታወቂያ አለመያዝ፣ ባልተፈቀደ በር መግባት፣ አትክልቶችን መርገጥና ማበላሸት፣ በቤተ-መጽሐፍት ውስጥ ለጓደኛ ቦታ መያዝና ከተቃራኒ ፆታ ጋር ተቃቅፎ መገኘት የቃል ማስጠንቀቂያ የሚያሰጡ ጥፋቶች ናቸው፡፡

በቤተ-ሙከራና ቤተ-መጽሐፍት ውስጥ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ ማስቲካ ማኘክና ሌሎች ተማሪዎችን ሊረብሹ የሚችሉ ነገሮችን ማድረግ፣ የተረፉ ምግቦችንና እጣቢዎችን በመስኮት መድፋት፣ ፍራሽ ወደ መሬት አውርዶ መጠቀምና ወደ ውጪ ማውጣት፣ ስዕሎችን መለጠፍ፣ ዶርም ይዞ ውጪ ማደርና ተከራይቶ መኖር፣ የምግብ ሰልፍ ሥርዓትን አለመጠበቅ፣ ወንበር እያለ ቆሞ መመገብ፣ ያለፈቃድ ወደ ማብሰያ ክፍል መግባትና ዶርም ለመመገብ መሞከር፣ በዩኒቨርሲቲው በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ ሁከት መፍጠር፣ አልኮል ጠጥቶ መግባት፣ በአጥር መዝለል፣ ፀጉርና ፂምን ከሥርዓት ውጪ ማሳደግና በንፅህና አለመያዝ የመጀመሪያ ደረጃ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የሚያሰጡ ጥፋቶች ናቸው፡፡

ከተማሪዎች ህብረት ፈቃድ ውጪ ገንዘብ ሲሰበስቡ መገኘት፣ የሌሎች ተማሪዎችን የትምህርት ዶክመንት መደበቅና ማበላሸት፣ ከውጤት ቅሬታ ጋር ተያይዞ የተሳሳተ ክስ እና ስም ማጥፋት በመምህራኖች ላይ መፈፀም፣ ሀይማኖታዊ አለባበስ ግቢ ውስጥ ለብሶ መገኘት፣ ከተፈቀደው ሰዓት ውጪ አምሽቶ መምጣትና ጥበቃዎች ጋር ችግር መፍጠር እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ያልተፈቀዱ ስልጠናዎችና ቲቶሪያል መስጠት ደግሞ የመጨረሻ ደረጃ ማስጠንቀቂያ ያሰጣሉ፡፡

የማህበሩ የጥናትና ምርምር ሂደት ሰብሳቢ የሆነው የህግ ተማሪ የአብሥራ ምንተስኖት ከባድ ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶችን አስመልክቶ ስልጠና ሰጥቷል፡፡ አንድ ዓመት ከሚያስቀጡ ጥፋቶች መካከል የሌላ ተማሪ መታወቂያና መመገቢያ ካርድ ይዞ ለመጠቀም መሞከር፣ የሀሰት የህክምና ማስረጃ ማቅረብ፣ በዶርም ውስጥ ህጋዊ ሳይሆኑ መግባትና የኤሌክትሪክ እቃዎችን መጠቀም፣ መሳደብ፣ ማስፈራራትና የድብደባ ሙከራዎችን ማድረግ፣ አደንዛዥ ዕፅ ወደ ግቢ ማስገባትና መጠቀም፣ ቁማር መጫወት፣ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ባህልና ማንነትን ማንቋሸሽ፣ ብሔርን መነሻ አድርጎ መሳደብ፣ በዩኒቨርሲቲው ንብረት ላይ ሆነ ብሎ ጉዳት ማድረስ፣ ለማሳደም መሞከር፣ ማሳደምና አድማ ላይ መሳተፍ፣ ሀሰተኛ ሰነድና መረጃ በመያዝ አገልግሎቶችን መጠየቅ፣ ፀብና ስም ማጥፋት ይጠቀሳሉ፡፡

የሥነ-ምግባር ቅጣት አፈፃፀምና እርምጃ አወሰሰድ፣ የሥነ-ሥርዓት ድንጋጌዎች፣ የክስ ሂደትና የውሳኔ አሰጣጥ፣ የክስ ማመልከቻ አቀራረብና የክስ መቃወሚያ፣ የውሳኔ አሰጣጥ፣ ክስና ቅጣት ማንሳትን አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያና ውይይት ተካሂዶበታል፡፡

ሰልጣኝ የ1 ለ 5 ቡድን ተጠሪዎች በሰጡት አስተያየት እንደቀላል የሚታዩ ነገር ግን ሊያስቀጡ የሚችሉ በርካታ መመሪያዎችን ከስልጠናው የተረዱ መሆናቸውን ገልፀው እንደ ህግ ተማሪነታቸው ህግና መመሪያው ተፈፃሚ እንዲሆን ያገኙትን ዕውቀት ለሌሎች የማስተላለፍ ትልቅ ኃላፊነት የሚጠበቅባቸው መሆኑንም ተናግረዋል፡፡