የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከኮሚዩኒቲ ት/ቤት ተማሪዎች፣ ወላጆችና ባለድርሻ አካላት ጋር በአንደኛ ወሰነ ትምህርት የተማሪዎች አፈፃፀም ዙሪያ መጋቢት 15/2010 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና የት/ቤቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደተናገሩት ውይይቱ የአንደኛ ወሰነ ትምህርት የተማሪዎች ውጤትና ሥነ-ምግባር ምን እንደሚመስል የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ያስችላል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የት/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሥላስ ጎዳና በበኩላቸው ተማሪዎች አመርቂ ውጤት እንዲያስመዘግቡና በመልካም ሥነ-ምግባር ታንፀው እንዲያድጉ ት/ቤቱ እየሠራ ይገኛል ብለዋል፡፡ ለውጤቱ መጠናከር ወላጆች ከት/ቤቱ ጎን በመቆም የድርሻቸውን በትጋት መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል፡፡

ተማሪዎችን በውጤትም ሆነ በሥነ-ምግባር የተሻሉ ለማድረግ ት/ቤቱ ከተማሪዎች፣ ከወላጆችና ከመምህራን ጋር በጥልቀት ውይይት ማድረጉን የተናገሩት የኮሚዩኒቲ 2ኛ ደረጃና መሰናዶ ት/ቤት ር/መ/ር አቶ ካምቦ ከተማ ሁሉም የየራሱን ድርሻ በመወጣቱ የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

አቶ ካምቦ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተመለከተው በመንፈቅ ዓመቱ የማጠቃለያ ፈተና ከወሰዱ የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ተማሪዎች መካከል 1 ወንድና 2 ሴት በድምሩ 3 ተማሪዎች ከ50% በታች ውጤት ሲያስመዘግቡ 168 ወንድና 163 ሴት በድምሩ 331 ተማሪዎች ከ50-74% አስመዘግበዋል፡፡ የቀሩት 40 ወንድና 29 ሴት በድምሩ 69 ተማሪዎች ከ75% በላይ አስመዘግበዋል፡፡ ውጤቱ በመቶኛ ሲሰላ ከ50 በታች 0.8% ፣ ከ50-74 ድረስ ያለው 82.1%  እና ከ75 በላይ 17.1% ነው፡፡

የኮሚዩኒቲ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት ር/መ/ር አቶ ከበደ ካሣ መምህራን አሳታፊ የማስተማር ሥነ-ዘዴን በመጠቀም፣ በክፍል ውስጥ የሚሰጠውን ትምህርት በትምህርት መርጃ መሣሪያ በማስደገፍ፣ የድጋፍ ትምህርት በመስጠት እንዲሁም የቤተ-ሙከራ፣ የቤተ-መጻሕፍትና የአይሲቲ አገልግሎቶችን አጠናክረው በመስጠት የማስተማር ሥራቸውን በትኩረት እየሠሩ መቆየታቸውን ገልፀዋል፡፡ በት/ቤቱ በማጠቃለያ ፈተና ላይ ከተቀመጡ 442 ተማሪዎች መካከል 5 ወንድና 4 ሴት በድምሩ 9 ተማሪዎች የት/ቤቱ የማለፊያ አማካይ ነጥብ ከሆነው 60 በታች ውጤት ሲያስመዘግቡ የቀሩት ተማሪዎች በሙሉ ከ60 በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን ር/መ/ሩ ተናግረዋል፡፡

የኮሚዩኒቲ ቅድመ መደበኛ ት/ቤት ር/መ/ር/ት ወ/ሮ ሣራ ጎይዳ በዕድሜ ለጋ ህፃናት በማንኛውም ጊዜ ከየትኛውም ህብረተሰብ ክፍል በበለጠ ለአደጋና ለጉዳት የተጋለጡ በመሆናቸው ልዩ ጥበቃ፣ አያያዝና እንክብካቤ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡ በቅድመ መደበኛ ትምህርት የአንደኛ ወሰነ ትምህርት ተከታታይ ምዘናን ከወሰዱ 226 ተማሪዎች 3 ወንዶችና 3 ሴቶች በድምሩ 6 ተማሪዎች ከ50% አማካይ በታች ውጤት ያስመዘገቡ ሲሆን የቀሩት ተማሪዎች ከ50% በላይ አማካይ ውጤት ማስመዝገባቸውን ር/መ/ርቷ ተናግረዋል፡፡

የተማሪዎቹ ወላጆች በሰጡት አስተያየት የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ለት/ቤቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ ለተማሪዎች ውጤት መሻሻል ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ጠቅሰው ለወደፊቱም ከት/ቤቱ ጎን በመቆም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ተማሪዎች፣ የተማሪ ወላጆች፣ መምህራንና የት/ቤቱ እና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አካላት የተሳተፉ ሲሆን በፕሮግራሙ ፍጻሜ ከየደረጃው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ሽልማት ተሰጥቷል፡፡