የተዘነጉ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምርምር ማዕከል በአ/ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ለተወጣጡ የጤና ክበብ ተጠሪ መ/ራንና ር/መ/ራን ከመጋቢት 24/2010 ዓ/ም ጀምሮ ለ3 ቀናት ትኩረት በሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች ምንነትና መከላከል፣ በውሃና የግል ንፅህና አጠባበቅ እንዲሁም በመፀዳጃ ቤት አጠቃቀም ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የማዕከሉ ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ገዝሙ እንደተናገሩት ትኩረት የሚሹ የቆላማ አካባቢ በሽታዎች በብዛት ህፃናትን የሚያጠቁ በመሆኑ ከህፃናት ጋር ለሚሠሩ መምህራንና ር/መምህራን ግንዛቤ በመፍጠር በሽታዎቹን የመከላከል ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ለማስቻል ሥልጠናው ተዘጋጅቷል፡፡ የግል፣ የአካባቢና የውሃ ንፅህናን በመጠበቅ በሽታዎቹን መከላከል ስለሚቻል እነዚህን ተግባራት ት/ቤቶቹ የዕቅዳቸው አካል አድርገው አንዲሠሩ ማዕከሉ ከዚህ በኋላ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም ገልፀዋል፡፡

በህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የውሃና ማህበረሰብ ጤና መምህርት አሠልጣኝ ገነት ገዳሙ እንደገለፁት ሠልጣኞች ያገኙትን ግንዛቤ ለተማሪዎች እና ለሌሎች መምህራን በማጋራት በበሽታዎቹ፣ በውሃና የግል ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ ያለውን የግንዛቤ ክፍተት መሙላት አለባቸው፡፡ በተለይ ርዕሰ መምህራን ህብረተሰቡን በማስተባበር በውሃና በሽንት ቤት አቅርቦትና ጥራት ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ፕሮጀክት ቀርፀው በቁርጠኝነት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አበክረው አሳስበዋል፡፡

የዚጊቲ ባቆሌ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ር/መ/ር አቶ ሙሉጌታ ሙቃ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት ከግልና ከአካባቢ እንዲሁም ከውሃ ንፅህና ጋር ተያያዥ ለሆኑ ሥራዎች ትኩረት ባለመስጠታችን ተማሪዎች ለተለያዩ በሽታዎች ሲጋለጡ የቆዩ ሲሆን በቀጣይ ጊዜያት ህብረተሰቡን በማስተባበር፣ በጀት በመመደብ እና ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ ግብአቶችን በማቅረብ ትኩረት ሰጥተን እንሠራለን ብለዋል፡፡

ሌሎች የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በሥልጠናው ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ተናግረው በበሽታዎቹ መከላከል ላይ የተፈጠረውን መዘናጋት ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተዋል፡፡

በሥልጠናው ቁጥራቸው 30 የሚሆኑ በአ/ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ የግልና የመንግሥት ት/ቤቶች የተወጣጡ መ/ራንና ር/መ/ራን የተሳተፉ ሲሆን በሥልጠናው ማጠናቀቂያ ለሠልጣኞች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡