ዩኒቨርሲቲው ከሴክሽን ተጠሪዎች፣ መምህራንና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በአንደኛ ወሰነ ትምህርት የሴክሽን ተጠሪ መምህራን ዝርዝር ተግባራት አፈፃፀም፣ የተመዘገቡ ስኬቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶች ዙሪያ ሚያዝያ 4/2010 ዓ.ም ውይይት አካሂዷል፡፡ ለውይይቱ መነሻ የተወሰኑ የሴክሽን ተጠሪ መምህራን ተሞክሮ ቀርቦ አስተያየት የተሰጠ ሲሆን እንደ ክፍተት የተወሰዱና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችም ተለይተው ውይይት ተደርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲዉ ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት በዩኒቨርሲቲው ውጤታማ አሠራርን ተግባራዊ ለማድረግ የሴክሽን ተጠሪ መምህራን ተማሪዎቻቸውን በእውቀት፣ በክህሎትና በመልካም ሥነ-ምግባር አብቅተው ለማስመረቅ ያልተገደበ ሀገራዊና ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ፡፡ የዚህ ውይይት ዓላማም በ2010 ዓ.ም 1ኛ ወሰነ ትምህርት በሴክሽን ተጠሪ መምህራን የተከናወኑ ተግባራትን በመገምገም፣ የተሻሉ ተሞክሮዎችን በማጋራትና ችግሮችን በመለየት ለ2ኛው ወሰነ ትምህርት ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ በበኩላቸው በሁሉም ዘርፎች የተሰማሩ ባለድርሻ አካላትና የሴክሽን ተጠሪ መምህራን ወቅቱን የጠበቀና ሰላማዊ መማር ማስተማር እንዲካሄድ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ በመሆኑ በወሰነ ትምህርቱ የተሻለ አፈፃፀም ተመዝግቧል ብለዋል፡፡

እንደ ዶ/ር የቻለ ገለፃ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሲወጡ የነበሩ የሴክሽን ተጠሪዎችና መምህራን እንዳሉ ሁሉ ያልተወጡም በርካታ ናቸው፡፡ በአንዳንድ መምህራን ዘንድ የማጠናከሪያ ትምህርትና ለሴቶች የሚሰጡ ድጋፎችን ከሠሩት በላይ ቁጥሩን ጨምሮ ሪፖርት ማድረግ፣ ተከታታይ ምዘናን በተገቢው ያለመስጠትና የመጀመሪያ ቀን የመጀመሪያ ክፍለ ጊዜን በትክክል ያለመተግበር ችግሮች ተስተውለዋል፡፡

በመድረኩ የውይይት መነሻ ተሞክሮ ያቀረቡት የ3ኛ ዓመት የጎፍኛ ቋንቋ ተማሪዎች ተጠሪ መ/ር ኢያሱ ማርቆስ እና የ2ኛ ዓመት የህግ ተማሪዎች ተጠሪ መ/ር ማሞ ገንጮ እንዳብራሩት የተማሪዎችን የትምህርትና የቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት አደረጃጀት መከታተልና መደገፍ፣ የተማሪዎችን አካደሚክ ፕሮፋይል ማደራጀት፣ የማማከር እንዲሁም የድጋፍና ክትትል ሥራዎች መከናወናቸው በወሰነ ትምህርቱ ለተመዘገበው የመማር ማስተማር ውጤታማነት የጎላ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ውይይቱ ጠቃሚ፣ ወቅቱን የጠበቀና ከፍተቶችን የሚለዩበት መሆኑን ጠቅሰው የአካዳሚክ ጉዳዮች ዘርፍ በትምህርት ክፍሎችና በእያንዳንዱ ሴክሽን የተከናወኑ ተግባራትን በዝርዝር መስፈርት አደራጅቶ መያዙ የሚያበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም እንደ ክፍተት የተወሰዱ ጉዳዮችን በ2ኛው ወሰነ ትምህርት በማሻሻል የበለጠ ውጤታማ ሥራ ለመሥራት መስማማታቸውን ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ዳይሬክተሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የት/ክፍል ኃላፊዎች እና  የክፍል ተጠሪዎች ተሳትፈዋል፡፡