የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ከሁሉም ካምፓሶች ለተወጣጡ የተማሪዎች ተጠሪዎች በሥነ-ምግባር ምንነት፣ በሙስና ፅንሰ ሃሳብ፣ በሙስና ወንጀል ምንነት እና የወንጀል ህጎች ላይ ሚያዝያ 14/2010 ዓ/ም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

የሥልጠናው ዓላማ ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናን የሚፀየፉ እና በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፁ ተማሪዎችን ለመፍጠር ግንዛቤ ማስጨበጥ መሆኑን የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ላቴኖ ላንጋና ገልፀዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የተለያዩ ምሁራን በሚሰጡት ትርጓሜ ሙስና ህግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመሥራት ይልቅ ሥልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ የህዝብን ሀብትና ንብረት በመስረቅ፣ በመዝረፍ፣ በማጭበርበር እንዲሁም በጉቦ፣ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በጎሰኝነት፣ በፖለቲካ ወገንተኝነትና በኃይማኖት ትስስር ላይ በመመርኮዝ ፍትህን እያዛቡ የግል ጥቅምን ማካበት እና ሌላን ወገን ተገቢ ባልሆነ መንገድ መጥቀም ወይም መጉዳት ነው፡፡

አቶ ላቴኖ  በሙስና ፅንሰ ሃሳብ ላይ ስልጠና ሲሰጡ እንደተናገሩት ሳይሰሩ በአቋራጭ የመክበር እና የተንደላቀቀ ሕይወት የመኖር ፍላጎት፣ የስርቆትና የስግብግብነት ባህሪይ፣ ለተለያዩ ሱሶች መጋለጥ እና ሌሎች መሠል ባህሪያት የሙስና መንስኤዎች ናቸው፡፡ የአፈፃፀሙ ሂደትና ስልት ውስብስብ መሆን፣ የፈፃሚዎቹ ማንነትና ምርመራውን የማደናቀፍ ወይም ፍሬቢስ የማድረግ ጥረት እንዲሁም በአብዛኛው ሰዎች ዘንድ እንደ ነውር አለመታየቱ ከሌሎች ወንጀሎች አንፃር ሲታይ የሙስናን አፈፃፀም ልዩ ያደርገዋል፡፡

አሠልጣኝ መ/ር ዮሃንስ ዳና በሥነ-ምግባር ምንነትና ፅንሰ ሃሳብ ላይ ስልጠና ሲሰጡ እንደገለፁት ሥነ-ምግባር በግል ሕይወት፣ በሕዝብ ወይም በመንግስት አገልግሎት የተጣለብንንና የሚጠበቅብንን አደራ ወይም ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት አለመወጣታችንን የምናረጋግጥበት ነው፡፡ የሰው ልጅ በአብዛኛው ማንነቱን የሚያገኘው በመከራ ጊዜ ቢሆንም በጥሩ ሥነ-ምግባር መመራት ከቻለ ፈታኝ ከሆኑ ነገሮች ራሱን ሊያድን ይችላል፡፡

ሠልጣኞች በአስተያየታቸው ስልጠናው በሥነ-ምግባርና ሙስና ፅንሰ ሃሳብ ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ከማዳበሩም በተጨማሪ ሙስናን የሚፀየፉ መልካም ዜጎች እንዲሆኑ እገዛው የላቀ ነው ብለዋል፡፡