በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና መጤ ባህሎች ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ

የሁሉ አቀፍ ሴክተር ዳይሬክቶሬት በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና መጤ ባህሎች ዙሪያ በሁሉም ካምፓሶች የግንዛቤ ማስጨበጫ የአሰልጣኞች ስልጠና ለተማሪዎች ሰጥቷል፡፡

የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር አቶ ታደሰ ዓለሙ ተማሪዎች በአፍላ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችና መጤ ባህሎች ሰለባ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በህክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የፋርማሲ ትምህርት ክፍል መምህር አሰልጣኝ መንዴ መንሳ እንደተናገሩት ጥቂት ተማሪዎች አደንዛዥ ዕጾችን መጠቀም ስኬታማ ያደርጋል በሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አደንዛዥ ዕጾችን ይጠቀማሉ፡፡ ነገር ግን አደንዛዥ ዕጾችን መጠቀም ከስኬት ርቀው ዝቅተኛ ውጤት እንዲያስመዘግቡ እና የአደንዛዥ ዕጾች ሱሰኛ እንዲሆኑ ስለሚያደርግ አስቀድሞ  መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የሁሉ አቀፍ ሴክተር የሥራ አካባቢ ጤንነትና ደህንነት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘላለም ንጋቱ የትምባሆ ምርቶች ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ እንዲሁም የጤና ችግር እንደሚያስከትሉ ገልጸዋል፡፡ ትምባሆን መጠቀም የልብ፣ የደም ስርና የመተንፈሻ አካል ህመሞችና ካንሰር እንዲሁም አካል ጉዳትንና ሞትን እንደሚያስከትል በሣይንስ የተረጋገጠ ስለሆነ ተማሪዎች ትንባሆን ከማጨስ መቆጠብ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎችን ከትምባሆ ጪስ ለመከላከል በሚደረግ የተግባር እንቅስቃሴ ውስጥ በመሳተፍ የትንባሆ ጪስ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለሌሎች ተማሪዎች ግንዛቤ ማስጨበጥ እንደሚኖርባቸው ባለሙያው ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ጠቃሚና ጥሩ ግንዛቤ የፈጠረላቸው መሆኑን ጠቅሰው በካፍቴሪያ፣ በመኝታ ክፍል፣ በስፖርት ማዘውተርያ ስፍራዎች፣ በ 1ለ5 ውይይት ጊዜና በሚገናኙበት አጋጣሚ ሁሉ ለሌሎች ተማሪዎች ስለአደንዛዥ ዕጾች አስከፊነት ግንዛቤ በመፍጠር ተማሪዎች እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡ ስልጠናው ቀጣይነት ቢኖረው፣ የተለያዩ አደንዛዥ ዕጾችን ለሚያከፋፍሉ ግለሰቦች ሌላ የሥራ አማራጭ ቢፈለግላቸውና ቁጥጥር ቢደረግ እንዲሁም ለ 2ኛ ደረጃና ኮሌጅ ተማሪዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ቢሰጥ የአደንዛዥ ዕጾች ስርጭትን ለመግታት እንደሚያስችል ሰልጣኞች ተናግረዋል::