የተማሪዎች የሥራ ፈጠራ ውድድር ተካሄደ

የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ማበልፀጊያ ማዕከል ሚያዝያ 16/2010 ዓ.ም የተማሪዎች የቢዝነስ ዕቅድ ውድድር አካሂዶ ለመጨረሻ ዙር አሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል፡፡

ውድድሩ በአንደኛው ወሰነ ትምህርት የተጀመረ ሲሆን ለተማሪዎቹ በተሰጠው የቢዝነስ ዕቅድ ስልጠና መሰረት የፈጠራ ሥራቸውን በማዘጋጀት በየኮሌጃቸው ተወዳድረው ለመጨረሻው ዙር ውድድር ደርሰዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የ3ኛ ዓመት የሆቴልና ቱሪዝም ማኔጅመንት ተማሪ አገኘው አስራት በ ‹‹Zengena mini Resort›› የቢዝነስ ዕቅድ 1ኛ በመውጣት አሸናፊ ሆኗል፡፡ የ4ኛ አመት የሜካኒካል ምህንድስና ተማሪ ሰለሞን መሳፍንት በ ‹‹Biotech Ethiopia›› የቢዝነስ ዕቅድ 2ኛ እና የ3ኛ ዓመት የመረጃ ቴክኖሎጂ ተማሪ ቦርናቶሊ ሙሉነህ በ ‹‹Online shopping Website›› የቢዝነስ ዕቅድ 3ኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ለተወዳዳሪዎች ባስተላለፉት መልዕክት በተማራችሁበትና በተዛማጅ የትምህርት መስክ ያካበታችሁትን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም ራሳችሁን፣ ወገኖቻችሁንና ሀገራችሁን ለማሳደግ የሚረዳ ልምድ ታጥቃችሁ መመረቅ ይገባችኋል ብለዋል፡፡ በውድድሩ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን መሳተፍ በራሱ የሚሰጠው ልምድ ለተማሪዎቹ የወደፊት እድገት ጠቃሚ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ይህን ውድድር እንደ መልካም ጅምር በመውሰድ በየዓመቱ የሚጠናከር ሲሆን ለሥራ ፈጠራ ተግባራት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ዩኒቨርሲቲው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የቢዝነስና ልማት/ም/ፕሬዝደንት ወ/ሮ ራሄል ኤልያስ በበኩላቸው ሥራ ፈጣሪነት በግለሰብና በአገር ደረጃ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት የሚያግዝ መሣሪያ መሆኑን ጠቅሰው እያንዳንዱ ጉዞ የሚጀምረው ከመጀመሪያው እርምጃ በመሆኑ ተወዳዳሪ ተማሪዎች ወደ ሥራ ፈጣሪነትና ሀብት ማግኛ መስመር ለመግባት የመጀመሪያ እርምጃችሁን ጀምራችኋል ብለዋል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎች ባገኙት ዕውቀት ሥራ በመፍጠር ለራሳቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለአገሪቱ ሀብት ማፍራት እንዲችሉ በማለም የዩኒቨርሲቲው የሥራ ፈጠራ ማበልፀጊያ ማዕከል በ2008 ዓ.ም ተቋቁሟል፡፡ ከምሥረታው ጊዜ ጀምሮም በሥራ ፈጣሪነትና የሥራ ፈጣሪነት ዝንባሌ፣ በቢዝነስ ዕቅድ አዘገጃጀት፣ በወጣት የሥራ ፈጣሪዎች መሰረታዊ የሥራ ፈጠራ ችሎታና ተወዳዳሪነት በመሳሰሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ለተማሪዎች ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷል ፡፡