የኦዲትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከልን ጨምሮ የሁሉንም ካምፓሶች የ2010 በጀት ዓመት 1ኛና 2ኛ ሩብ ዓመት የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በግዥና ንብረት አስተዳደር የ3ኛ ሩብ ዓመት የአላቂ እቃዎች አጠቃቀም ኦዲት ሪፖርትን አስመልክቶ ሚያዝያ 22/2010 ዓ/ም ጉባኤ አካሂዷል፡፡ በሪፖርቱ በተገለፁ ግኝቶች፣ ስጋቶችና የማሻሻያ ሃሳቦች ዙሪያም ውይይት ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

 

የጉባኤው ዓላማ የፋይናንስና በጀት እንቅስቃሴዎች የመንግስትን ህግና መመሪያ የተከተሉ መሆናቸውን በመገምገም ክፍተት የታየባቸው የሥራ ክፍሎች ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንዲመጡ ማስቻል  መሆኑን የኦዲትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ተረፈች መንግስቱ ገልፀዋል፡፡

በኦዲትና ኢንስፔክሽን ዳይሬክቶሬት የፋይናንስ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሙላቱ ደጀኔ ባቀረቡት ሪፖርት እንደተመለከተው አግባብነት የሌለው የውሎ አበል አከፋፈል፣ ከተቋሙ ዕቅድ ውጪ ግዥዎችን መፈፀም፣ የንግድ ፈቃድ ያላደሱ የንግድ አካላትን በግዥ ጨረታ ውስጥ ማሳተፍ እንዲሁም ቋሚና አላቂ እቃዎችን ለረጅም ጊዜ ያለ አገልግሎት ማቆየት ከታዩ  ክፍተቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በተቋሙ የውስጥ ገቢም ሆነ በማናቸውም መንገድ የሚሰበሰብ የመንግስት ገንዘብ በውቅቱ ወደ ባንክ ገቢ ማድረግ፣ ወጪና ገቢ የሚደረጉ ማናቸውንም የመንግስት ንብረቶች ህግና መመሪያውን በመከተል ተግባራዊ ማድረግ እንዲሁም ግዢዎችን በወቅቱና በተገቢው መንገድ ማከናወን ሊሻሻሉ ከሚገባቸው ነጥቦች መካከል ተጠቅሰዋል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የተቋሙን የሂሳብ ሪፖርት እንዲሁም የመንግስት የበጀት አጠቃቀምን ሊጎዱ ከሚችሉ ነገሮች በመቆጠብ የፋይናንስ ግልፀኝነትና ተጠያቂነት ላይ የተሻለ እንደሚሠሩ ገልፀዋል፡፡

በጉባኤው የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ ዳይሬክተሮች እንዲሁም የኮሌጅና የኢንስቲትዩት የፋይናንስ፣ የግዥና የንብረት አስተባባሪዎች ተሳትፈዋል፡፡