የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ከዩኒቨርሲቲው አመራሮችና ከጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር በዞኑ የቱሪስት መረጃ ማዕከል ግንባታ፣ በወዜ ሻራ የተፋሰስ ሥራ እና በቤሬ ተራራ መልሶ ማልማትና ማካለል ላይ መጋቢት 26/2010 ዓ.ም ውይይት አድርጓል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ለቱሪስቶች የተደራጀና ቀልጣፋ መረጃ የሚሰጥ ማዕከል በማቋቋም የዞኑንና የከተማውን በጎ ገጽታ ለመገንባት እንዲሁም የተጎዳ ሥነ-ምህዳር ያላቸውን ቦታዎች መልሶ በማልማት የአካባቢውን ህብረተሰብ ከሚደርስበት አደጋ ጠብቆ ዘላቂ ተጠቃሚ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ከዞኑ ጋር ተቀናጅቶ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ላይ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ውይይቱ ተዘጋጅቷል፡፡

የቱሪስት መረጃ ማዕከሉ ዲዛይን ባለ 3 ፎቅ ሲሆን የእንግዳ መቀበያ፣ ካፍቴሪያ እና አነሰተኛ የመሰብሰቢያ አዳራሽን ጨምሮ የተለያዩ ቢሮዎችን ማካተቱን የሥነ-ህንፃና ከተማ ፕላን ት/ክፍል መምህር አቶ ቤዛዬ ቦጋለ ገልፀዋል፡፡ የህንፃው ሳኒታሪና ስትራክቸራል ዲዛይን በቀጣይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃልም ብለዋል፡፡

ሌላው የት/ክፍሉ መምህር አቶ ታደሰ መንበሩ ህንጻው 250 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ መሆኑን ገልፀው ህንጻው ሲጠናቀቅም በተለይ የአካባቢውን ነዋሪዎች በብዙ መልኩ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ ማዕከሉን ለማቋቋም የነበሩትን በርካታ ተግዳሮቶች በማለፍ ወደ ተግባር ለመግባት የህንፃው ዲዛይን መጠናቀቁ የሥራው ጅማሮ አንዱ አካል ነው ብለዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከዞኑ ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያ ጋር በየጊዜው በመገናኘት ዞኑን ለቱሪስት መስህብነት ተመራጭ ለማድረግ እንደሚጥር ዶ/ር መልካሙ ጠቁመዋል፡፡

የልማት ሥራዎች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደፋሩ ደበበ ዩኒቨርሲቲው የወዜ ሻራ ተፋሰስን ለማልማት ላለፉት 5 ዓመታት ሰፊ ሥራ ሲሠራ መቆየቱንና አሁንም በመስራት ላይ መሆኑን ገልጸው MIBC (MAINSTREAMING INCENTIVES FOR BIODIVERSITY CONSERVATION) የሚባል ድርጅት ከ2008 ዓ.ም ሰኔ ወር ጀምሮ በሥራው መሳተፉ  የቦታውን መራቆት በከፊል እንዲለማና እንዲያገግም አድርጎታል ብለዋል፡፡ በአንፃሩ የቤሬ ተራራ እጅግ በመጎዳቱና በመራቆቱ የወዜ ተፋሰስ ላይ የነበረውን የዩኒቨርሲቲውን ፕሮጀክት ወደ ቤሬ ተራራ ሙሉ በሙሉ ማዛወር ማስፈለጉን ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የወዜ ሻራ ተፋሰስን ለማልማት የወሰደውን ኃላፊነት ለዞኑ አካባቢ ጥበቃና ደን  ልማት  ጽ/ቤት መስጠቱን የውይይቱ አስተባባሪና የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ገልፀዋል፡፡ አዲሱን ፕሮጀክት አጠናክሮ ለመቀጠል ዩኒቨርሲቲው ከጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደርና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የልማት ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ ይሠራል ብለዋል፡፡

በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮችና ከዞኑ የተለያዩ የሥራ ክፍሎች የተወጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡