ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ ከጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደርና ከጋሞ ጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የተወጣጡ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በጋሞ ጎፋ ዞን ጨንቻ ወረዳ ወበራ ጤና ጣቢያ፣ በደንባ ጎፋ ወረዳ ላይማ ጻላ ጤና ጣቢያና ላይማ ጻላ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት የተሠሩ የታዳሽ ኃይል ሥራዎች የመስክ ምልከታ ከግንቦት 18-19/2010 ዓ.ም አካሂደዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ሥራዎች መካከል አንዱ የሆነው የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት ሥራ ምን ያህል የህብረተሰቡን ችግር እየፈታ መሆኑን ከተጠቃሚዎች በተጨባጭ ለማረጋገጥ እና በፕሮጀክቱ ቀጣይነት ዙሪያ ከዞኑና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ለመወያየት የመስክ ምልከታው መዘጋጀቱን የዩኒቨርሲቲው የታዳሽ ኃይል ቴክኖሎጂ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተርና የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት አሰተባባሪ  አቶ ዘላለም ግርማ ገልፀዋል::

የጋሞ ጎፋ ዞን አስተዳደር ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት አማካኝነት ከ2008-2010 ዓ.ም ድረስ በዞኑ የሚገኙ 18 ጤና ጣቢያዎች የ24 ሰዓት የሶላር መብራት አገልግሎት ያገኙ ሲሆን በተጨማሪም 3 ጤና ጣቢያዎችና ሁለት የ2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አቶ ዘላለም ተናግረዋል፡፡ በእያንዳንዱ ጤና ጣቢያ የሚገኘው የሶላር ሲስተም አጠቃላይ ወጪ 1 ሚሊየን ብር የፈጀ ሲሆን የኃይል መጠኑ 5 ኪሎዋት ሆኖ  ባትሪው ከ7-10 ዓመት፣ ኢንቨርተሩ ከ15-20 ዓመትና ሶላር ፓናሉ እስከ 30 ዓመት አገልግሎት መስጠት ይችላሉ፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪና የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት ተጠሪ አቶ ግባዬ ግልጮ እንደተናገሩት የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቱ ለጤና ጣቢያዎችና ለት/ቤቶች የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ የህብረተሰቡን ችግር ከመቅረፍ አኳያ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡ በቀጣይ ዞኑ ለወረዳ አመራሮች ኦረንቴሽን በመስጠት በጋራ በትኩረት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማኅበረሰብ አገልገሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ የሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት በጋሞ ጎፋ ዞን የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ያከናወናቸው የታዳሽ ኃይል ሥራዎች ለአካባቢው ማህበረሰብ ከጠበቅነው በላይ አመርቂ አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑ ሊበረታታና ሊደነቅ ይገባል ብለዋል፡፡ የፕሮጀክት ሥራውን ለማሳካት የጋራ ጥረት የሚጠይቅ በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የደምባ ጎፋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢያሱ ጣሰው በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው ህብረተሰብ ያከናወነውን ሥራ በማድነቅ በጤናው ዘርፍ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የፕሮጀክቱ ሥራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሶላር ኃይል አገልግሎት ለጤና ጣቢያዎች ከማስገባቱ በፊት ከከተማ ርቀው በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች አገልግሎት ለመስጠት በጣም አስቸጋሪ ነበር ያሉት የጋሞ ጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የጤና አገልግሎቶች ኦፊሰር ሲ/ር ትዕግስት ታደሰ የሶላር ኃይል ከገባ ወዲህ በላቦራቶሪ የታገዘ ጥራት ያለው አገልግሎት በመስጠት የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

የወበራ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሳሬ እና የላይማ ጻላ ጤና ጣቢያ ኃላፊ አቶ አብድኬ አዶላ እንደተናገሩት የሶላር ኃይሉ ለታካሚዎች ቀልጣፋና አመርቂ አገልግሎት ለመስጠት፣ እናቶችን ለማዋለድ፣ በቅድመ ወሊድ ወቅት ነፍሰ ጡር እናቶችን በማቆያ ስፍራ ለመከታተል፣ በጤና ጣቢያ ውስጥ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ማናቸውንም ሥራዎች ያለማቋረጥ ለማከናወን አስችሏል፡፡ የአካባቢው ህብረተሰብ የስልክና የእጅ ባትሪ ቻርግ አገልግሎት እንዲያገኝም አድርጓል፡፡

የላይማ ጻላ 1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤቶች ርዕሳነ መምህራን አቶ አየለ ዝግሌ እና አቶ ጃርሰው ቶሜ በበኩላቸው በት/ቤታቸው የሶላር ኃይል ከገባ ወዲህ መምህራን ለተማሪዎች እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት የድጋፍና ማጠናከሪያ ትምህርት በመስጠት፣ የኮምፕዩተር አጠቃቀም መሰረታዊ ግንዛቤ በማስጨበጥ እንዲሁም የእንግሊዝኛ ቋንቋና ሌሎች ትምህርት አይነቶችን በካሴት ቀርጸው በማስተማር ተማሪዎች የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ አስችሏል ብለዋል፡፡

አስተያየት የሰጡት የአካባቢው ነዋሪዎች የሶላሩ ተጠቃሚ ከመሆናቸው በፊት ለህክምና ወደ ጤና ጣቢያዎች በሚመጡበት ወቅት አስፈላጊውን የህክምና አገልግሎት ለማግኘት እንደሚቸገሩ ገልፀው አሁን የሚያገኙት አገልግሎት አስደሳችና ቀልጣፋ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ባለሙያዎች መብራት ባለመኖሩ ከቦታው በፍጥነት የመዛወርና የመብራት ኃይል አገልግሎት ለማግኘት ወደ ከተማ መመለስን አቁመው ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በመስክ ምልከታው የተገኙ የዩኒቨርሲቲውና ሌሎች ተጋባዥ አመራሮች የተመለከቱት ሥራ በጣም እንዳረካቸውና የህብረተሰቡን ችግር በተጨባጭ የፈታ መሆኑን ተናግረው ሥራው ቀጣይነት እንዲኖረው የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ እንዳይቀንስ አሳስበዋል፡፡