ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለተወጣጡ መምህራን ስልጠና ተሰጠ

የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት በዩኒቨርሲቲው ክላስተር ሥር ካሉ ስምንት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ለተወጣጡ መምህራን ከሚያዚያ 30- ግንቦት 2/2010 ዓ/ም በዘላቂ የእሴት ሰንሰለት አቀራረጽ ዙሪያ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ስልጠናው በሴክተር ልማት የእሴት ሰንሰለት ባሉ መልካም አጋጣሚዎችና ተግዳሮቶች ዳሰሳ ለማድረግ፣ በገበያና በአቅርቦት እሴት ሰንሰለት ልማትና ቀጣይነት ላይ መፍትሄ  ማምጣት የሚችል አቅም ለመፍጠር፣ በግብርና ምርትና ምርታማነት ላይ የእሴት ሰንሰለት ዘዴና የእድገት መሥመር እንዲሁም ኋላቀር የሆነውን የምርት ሥርዓት በማዘመን ውጤታማ አሠራር ለመፍጠር ብሎም በዩኒቨርሲቲውና በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆቹ መካከል የተጀመረውን ትስስር በመጠቀም በእሴት ሰንሰለት ትንተና ጥናት ላይ ጠንካራ ሥራ ለመሥራት የሚያስችል መሆኑን የዩኒቨርሲቲ-ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ የሚሠሩ የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎችን በትክክል ለማሻገር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

የእሴት ሰንሰለት ምንነትና ይዘት፣ የዘርፉ መመሪያዎችና መስፈርቶች፣ የግብርና እሴት ሰንሰለት ገጽታ፣ የገበያና የአቅርቦት ትስስር፣ የእሴት ሰንሰለት ካርታና ቀጣይነት ያለው የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ትንተና እንዲሁም የእሴት ሰንሰለት ዙሪያ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር መብራቱ ዓለሙ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያ ተሳታፊዎች በስልጠናው ባገኙት ሀሳብ መነሻነት የራሳቸውን አነስተኛ የእሴት ሰንሰለት ፕሮጀክት ሠርተው ያቀረቡ ሲሆን ይህም ከሥልጠናው በኋላ ወደ መጡበት ተቋም ሲመለሱ በቀላሉ መተግበር እንዲችሉ ለማድረግ እንደሚረዳ ተገልጿል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ በአካባቢውና በአጎራባች ወረዳዎች ከሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እና ከማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪዎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት በማድረግ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመሥራት፣ ባለሙያዎችን በስልጠና ለማብቃትና ድጋፍ ለመስጠት፣ ቴክኖሎጂውን በማሸጋገር በዘርፉ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግና የሥራ ዕድል ለመፍጠር እንዲሁም ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ ገበያ ለመወዳደር ከሚያስችላት የአቅርቦትና የጥራት ደረጃ ለማድረስ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል፡፡

ለሦስት ተከታታይ ቀናት በተሰጠው ስልጠና በዩኒቨርሲቲው ቀጠና ሥር ከተሳሰሩ ስምንት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የተወጣጡ 16 ሰልጣኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡