ለሴት የምክር ቤት አባላት በአመራርነትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ስልጠና ተሰጠ

የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ እና የማህበራዊ ሣይንስና ሥነ- ሰብ ኮሌጆች የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች ከጋሞ ጎፋ ዞን ምክር ቤት ጋር በመቀናጀት ለዞኑ የክልልና የዞን  ምክር ቤት ሴት አባላት እንዲሁም ለዞኑ 15 ወረዳዎችና 2 የከተማ አስተዳደሮች ዋናና ምክትል አፈ-ጉባኤዎች በድምሩ ለ80 ሰልጣኞች ከግንቦት 13 - 16/2010 ዓ/ም በአመራርነትና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ላይ ስልጠና ሰጥተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የሠራተኛ አመራር፣ የሥራ ክፍል ራዕይና ተልዕኮ ቀረፃ፣ ውሳኔ ሰጪነት እና የግጭት አፈታት በስልጠናው ከተዳሰሱ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ስልጠናው በአመራርነት ሙያ ላይ ያሉ ሴቶችን ብቃት በማጎልበት ለሌሎች ተምሳሌት የሚያደርግና ወደ አመራርነት የሚመጡ ሴቶችን ተሳትፎ የሚያሳድግ መሆኑን የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ አስተባባሪዎች ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በአካባቢው እየተካሄዱ ያሉ ጎጂ ልምዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የሚያስችል ግንዛቤን ይፈጥራል ብለዋል፡፡

አሰልጣኝ ረ/ፕሮፌሰር አብዮት ፀጋዬ እንዳብራሩት አመራርነት የአንድን ተቋም ራዕይና ተልዕኮ በመቅረጽ፣ አቅጣጫውን በሚገባ በመገንዘብና ሌሎችም እንዲያውቁ በማድረግ፣ ተቋሙ ቀድሞ የነበረውን ታሪካዊ ዳራ በመለየትና አሁን ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም እንዲሁም የወደፊት ግቡን በማስቀመጥ በሥሩ ያሉትን ሠራተኞች ከፊት ሆኖ መምራትና ተቋሙን ወደተሻለ ደረጃ ማድረስ ነው፡፡

እንደ አሰልጣኙ ገለፃ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት የአመራርነት ዕውቀታቸውን ማሳደግ፣ አቅማቸውን ማጎልበት እንዲሁም ለራሳቸው ያላቸውንና ሌሎች ስለእነርሱ ያላቸውን አመለካከት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም ባሻገር መንግሥት ሴቶችን ለአመራርነት ለማብቃት በተለያዩ መድረኮች ማበረታታት፣ የሥነ- ልቦና ግንባታዎች ማከናወንና ውጤታማ ከሆኑ ሴቶች ጋር ልምድ እንዲለዋወጡ መድረክ ማመቻቸት ይገባዋል፡፡

የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ቃንጨሮ ቃንጬ እንደገለፁት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የጤና ጉዳት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የሚያስከትሉ ናቸው፡፡ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ሴት ልጅን እንደ ልጅ አለመቁጠር፣ ድርብ ጋብቻ፣ የውርስ ጉዳይ የመሳሰሉት በህግ የተከለከሉ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በአሁኑ ወቅት የቀነሱ ቢመስልም በክልሉ በብዛት እየተፈፀሙ እንደሚገኙም ጠቁመዋል፡፡

ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች መካሄዳቸውን የገለፁት የሶሲዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ሳልህ ሰይድ አስቀድሞ ከመከላከል አንፃር የማህበረሰቡን አመለካከትን የመቀየር፣ የህግ ከለላ ወይም ሽፋን የመስጠት እና ወንጀልነቱን አውቀው ከድርጊቱ እንዲርቁ የማድረግ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በተጨማሪም መዋቅር በመዘርጋት የሴቶችና ህፃናት፣ የትምህርት እና የጤና ቢሮዎች፣ የተለያዩ ፎረሞች እና በቀበሌ ደረጃ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች አስወጋጅ ኮሚቴ ተቋቁሞ ኃላፊነት ወስደው እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡

ድርጊቶቹ ከተከሰቱ በኋላ ተፅዕኗቸውን ለመቀነስና በቀጣይ እንዳይደገሙ ለማድረግ በህጋዊ መንገድ በገንዘብና በእስር የመቅጣት፣ ለሴቶችና ህፃናት የምክር አገልግሎት የመስጠት እንዲሁም መልሰው ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ የማድረግ ስራዎች መሠራታቸው ተገልጿል፡፡

ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት የአመራርነት ክህሎታቸውን በማጎልበትና በመጠቀም የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ በትክክለኛው መንገድ ለማሳካት ስልጠናው ፈር ቀዳጅ መሆኑን ገልፀው በተሰጣቸው ኃላፊነት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስቀረት በየወረዳዎችና ት/ቤቶች ላይ ህብረተሰቡን የማወያየትና የማስተማር ሥራ እንደሚሠሩና ክትትል እንደሚያደርጉም ገልፀዋል፡፡

ሴቶች ቤትን ከማስተዳደር ጀምሮ በተሰማሩበት የሥራ መስክ ባላቸው ኃላፊነት ውጤታማ ሊሆኑ ይገባል ያሉት የጋሞ ጎፋ ዞን ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባኤ ወ/ሮ ልሳነወርቅ ካሳዬ ሰልጣኞች የዞንና የክልል ምክር ቤት አባላት እንደመሆናቸው የህዝብ ውክልና እና የህግ አውጪው አካል ትልቅ ውሳኔ ላይ ድርሻ ያላቸው ስለሆኑ በዕውቀት የተሞላና ከወቅቱ ጋር የሚመጣጠን አመራርነት መስጠት እንዲችሉ አቅማቸውን ማጎልበት ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ራሳቸውን ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በማቀብና ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ በመሆን ኃላፊነታቸውን ተጠቅመው በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጎጂ ልማዳዊ ተግባራትን መዋጋት አለባቸው ብለዋል፡፡