“የቡና ዝርያ ማሻሻያና አጠቃቀም፣ ምርምርና ቴክኖሎጂ” የምርምር ፕሮጀክት አፈፃፀምና የጥናት ግኝት ላይ የመስክ ጉብኝት ተካሄደ

በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲና በጅማ የእርሻ ምርምር ማዕከል ትብብር በጋሞ ጎፋ ዞን ከሚገኙ የቡና አብቃይ ወረዳዎች አንዱ በሆነው በደንባ ጎፋ ወረዳ ሱካ ቀበሌ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲካሄድ በነበረው የቡና ዝርያ ማሻሻያ ምርምር ፕሮጀክት ጣቢያ የሥራ እንቅስቃሴ ምልከታ፣ አፈፃፀምና የጥናት ግኝት ላይ ከግንቦት 25-26/2010 ዓ/ም የመስክ ጉብኝትና የምርምር ውጤቶች ትውውቅ ተካሂዷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የመስክ ጉብኝቱ ዓላማ በዞኑ በሚታወቁ አራት ቡና አብቃይ ወረዳዎች በተደረጉ ጥናቶችና ከባቢያዊ ሥነ-ምህዳር ዓይነቶች መነሻ ነባሩን የአካባቢ ዝርያ ‹‹ሞጴ›› ጨምሮ በሌሎች ሦስት ዝሪያዎች ምርምር ውጤቶች ላይ ምልከታ ማድረግና ቀደም ሲል በአካባቢው ያለውን የአመራረት ዘዴና አፈፃፀም ዝርዝር ማወቅ ነው፡፡ በዚህም ተመሳሳይ ሥነ-ምህዳር ያላቸውን በመውሰድ ከአካባቢዎች ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ በመተግበርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሩና የንግዱ ማህበረሰብ በዘርፉ ተጠቃሚነቱን እንዲያሰፋ ግንዛቤ ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የብዝሃ-ህይወት ማዕከል ዳይሬክተርና የዘርፉ ተመራማሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ሰይፉ ፈቴና ገልፀዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በመክፈቻ ንግግራቸው በግብርናው መስክ ቡና ያለው ሚና ከፍ ያለና በውጪ ምንዛሪም ረገድ የላቀ ድርሻ የያዘ ቢሆንም ዘርፉ ለአርሶ አደሩም ሆነ እንደ ሀገር ጥቅም ሊሰጥ የሚገባውን ያህል አለመሆኑን አውስተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት ዘርፉን በጥናትና ምርምር ማገዝና ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በዘርፉ የሚታየውን ችግር ቀርፎ የቡና ምርትና ምርታማነት ለሀገር የሚሰጠውን ጥቅም በማሳደግ ህዝቡን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በሚደረገው ርብርብ በዞኑ ቡና አብቃይ አካባቢዎች ከፍተኛ በጀት በመመደብ    ዘርፉን በምርምር ለማገዝ እየሠራ መሆኑን ዶ/ር ስምኦን አረጋግጠዋል፡፡

በደንባ ጎፋ ወረዳ ለቡና ልማት ምቹ ሥነ-ምህዳርና ሊለማ የሚችል ሰፊ መሬት ያለ ሲሆን የቡና ምርትም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ካላቸው ሰብሎች በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡ ነገር ግን አርሶ አደሩ ተለምዷዊ አሠራርን ተከትሎ በማምረቱና በጥናትና ምርምር የተደገፈ ምርጥ ተሞክሮ ማስፋፋት ባለመቻሉ ተጠቃሚነቱ እምብዛም ሆኖ መቆየቱን የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ያይቆብ ቦቴላ ገልፀዋል፡፡

የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው የቡና ምርት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት ባለፈ 25 በመቶ ለሚሆነው ህዝብ የኑሮ መሠረት መሆኑን በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እንዲህም ሆኖ ዘርፉ በጥናትና ምርምር ባለመደገፉ በዝርያ አጠቃቀምና በምርት አያያዝ ችግር በሚጠበቀው ደረጃ ውጤታማ ሆኖ ኢኮኖሚውን መደገፍ ያልቻለ ሲሆን ሽፋኑም በተወሰኑ አካባቢዎች ብቻ የተገደበ እንደሆነ የፕሮጀክቱ ተመራማሪዎች አስገንዝበዋል፡፡

እንደ ተመራማሪዎቹ ገለፃ በቡና አብቃይ ወረዳዎች የሚታየው የቡና ምርትና ምርታማነት ከ5-6 ኩንታል በሄክታር ሲሆን ይህም በብሔራዊ ደረጃ ካለው ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ የሚባል ነው፡፡ ለዚህም በአርሶ አደሩ ጓሮ የተተከሉ ጥቂት የቡና እናት ዛፎች ነባር ዝርያዎች በመሆናቸው በቀላሉ በበሽታ መጠቃታቸው፣ አካባቢን መላመድ የሚችሉና ምርትና ምርታማነት የሚጨምሩ አለመሆን እንዲሁም በቂና የማያቋርጥ የዘር ምንጭ አለመኖር በዋናነት የዘርፉ እንቅፋት እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡ አዲስ የተሻሻሉ ዝርያዎች ከዘር ዝግጅት ጀምሮ አራት ዓመት ተኩል የሚወስዱና በተተከሉ በሦስተኛ ዓመታቸው ምርት መስጠት የሚጀምሩ ሲሆን ከአራቱ ዝርያዎች በተለይም ለቆላማ አካባቢ ምቹ የሆኑት F-59(ደሱ) እና 1377(አንጋፋ) የተባሉ በዓመት ሁለት ጊዜ ምርት የሚሰጡና በሄክታርም ከ12-25 ኩንታል ምርት ማምረት የሚያስችሉ ናቸው፡፡

በመስክ ጉብኝቱ የተገኙ ሞዴል አርሶ አደሮች በሰጡት አስተያየት በቡና ምርት ሂደት የዝርያ አማራጭ አጠቃቀም በዕውቀትና በሣይንሳዊ መንገድ ሳይደገፍ ለዘመናት በመተግበሩ ምርትና ምርታማነቱ ላይ አያሌ ችግሮች እንደገጠሟቸውና ውጤታማም እንዳልነበሩ ገልፀው በአካባቢያቸው በተቋቋመው የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጣቢያ የታየው ውጤትና የዘር አማራጭ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡ ወደየቀበሌያቸው ሲመለሱም ያገኙትን ግንዛቤ ለሌሎች ለማጋራትና የዘር ማፍላቱ ሥራ ተጠናቆ ሲሠራጭ ለመጠቀምና ምርታማ ለመሆን ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠው ለዚህም የዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እንዳይለያቸው አጽንዖት ሰጥተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ከ2005 ዓ/ም ጀምሮ ከ400 ሺህ ብር በላይ በሆነ በጀት ካምባን ጨምሮ በዞኑ አራት ወረዳዎች ስድስት የምርምር ጣቢያዎች እየተካሄደ ይገኛል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የምርምር ዳይሬክቶሬት በተዘጋጀው የመስክ ጉብኝት ቀን የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ ተመራማሪዎች፣ ከዞንና ወረዳ ቢሮዎች የተወከሉ ባለሙያዎችና ሞዴል አርሶ አደሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡