የዓለም አካባቢ ቀን አከባበርን ምክንያት በማድረግ ከዩኒቨርሲቲው፣ ከጋሞ ጎፋ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ጽ/ቤት፣ ከ15ቱ ወረዳዎችና ከአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር የተወጣጡ አመራሮችና የአካባቢው ማኅበረሰብ ግንቦት 28/2010 ዓ.ም በቤሬ ተፋሰስ የችግኝ ተከላ አካሂደዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የማኅበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የሀገር በቀል ችግኞች ተከላው አካባቢውን መልሶ ለማልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው ችግኞቹን በአግባቡ በመጠበቅና በመንከባከብ ለአርባ ምንጭና አካባቢዋ ተገቢውን ጥቅም በዘላቂነት እንዲሰጡ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ከዞኑ አካባቢ ጥበቃና ደን ጽ/ቤት ጋር በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

የጋሞ ጎፋ ዞን አካባቢ ጥበቃና ደን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ኩማ በበኩላቸው በአሁኑ ጊዜ የቴክኖሎጂ ዕድገት፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የመሬትን ተፈጥሯዊ ባህሪ ያልተከተለ የእርሻ መስፋፋት፣ በከፍተኛ ሁኔታ የደን መመንጠር፣ ልቅ የእንስሳት ግጦሸ እና የፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎች አወጋገድ ስልታዊ አለመሆን አካባቢን እየበከለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሁሉም ህብረተሰብና ተቋም አካባቢውን ለማልማትና ለመጠበቅ ቁርጠኛ እንዲሆንም አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ ‹‹አካባቢያችንን ከፕላስቲክ ብክለት እንከላከል›› በሚል መሪ ቃል በሰነዶች መነሻነት የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በሰነዶቹ እንደተብራራው አካባቢን ለመጠበቅ በአካባቢው የሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ እየደረሱ ያሉ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን በመተንተን መንስኤዎችንና አማራጭ መፍትሄዎችን መለየት፣ የልማትና የፍትሃዊ አጠቃቀም ሥርዓት በማበጀት ተገቢውን የቁጥጥር፣ የክትትልና ግምገማ እቅድ ማዘጋጀት እንዲሁም ለተግባራዊነቱ በኃላፊነትና በተጠያቂነት መሥራት ይጠይቃል፡፡ በተጨማሪም የደረቅና ፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል፡፡

ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት አካባቢያቸውን መጠበቅ የሞት ሽረት ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ሰው ወደ ተግባር በመግባት የተተከሉትን ችግኞች መንከባከብ እንዲሁም ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎችን በተገቢው ማስወገድ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በፕሮግራሙ ፍፃሜ በአካባቢ ጥበቃ የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅናና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡