በተማሪዎች የተሠሩ ሶፍትዌሮች ለዕይታ ቀረቡ

የኮምፒውተር ሣይንስ እና ሶፍትዌር ምህንድስና ፋከልቲ ተማሪዎች ክበብ ግንቦት 22/2010 ዓ/ም 7ኛውን ዙር የአይ.ሲ.ቲ ፌስቲቫልና ዓውደ ርዕይ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ አካሂዷል፡፡

የዓውደ ርዕዩ ዓላማ የፋከልቲው ተማሪዎች በክፍል ውስጥ ባገኙት እውቀትና ክህሎት የሠሯቸውን ችግር ፈቺ ፕሮጀክቶች ለሌሎች በማሳየት ልምድ የሚያካፍሉበትና ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ያላቸውን አቅም የሚያሳዩበት መድረክ መፍጠር ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ፕሮግራሙ ስለ ኮምፒውተር ሣይንስ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሶፍትዌር ምህንድስና በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ግንዛቤ የሚያሰፋ፣ ለሌሎች ተማሪዎች መነሳሳትና መነቃቃትን የሚፈጥር እና ፋከልቲውን በይበልጥ ለማስተዋወቅ የሚረዳ መሆኑን የፋከልቲው ኃላፊ አቶ መሳይ ሳሙኤል ገልፀዋል፡፡

በተለያዩ ወቅቶች በተማሪዎች የተሠሩ መሰል ፕሮጀክቶች ተስፋ ሰጪና ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ቢሆኑም ተማሪዎች ተመርቀው ሲወጡ ኃላፊነት የሚወስድ አካል ባለመኖሩ ውጤታማ ሊሆኑ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡ ይህንን ለመቅረፍ ትምህርት ክፍሉ ከተመሰረተ ጀምሮ መምህራንን በመመደብና ድጋፍ በመስጠት የክበቡን እንቅስቃሴ ከማገዝ አልፎ ሥራዎቹ ወደ መሬት ወርደው አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እንደሚሠራም አቶ መሳይ ገልፀዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ ‹‹online maternal health advice››፣ ‹‹job site››፣ ‹‹city and location guides››፣ ‹‹Telecommunication apps››፣ ‹‹Book renting›› ሶፍትዌሮችን ጨምሮ 10 የፈጠራ ፕሮጀክት ሥራዎች ቀርበው በተሳታፊዎች ተጎብኝተዋል፡፡

በተማሪዎች የቀረቡት እነዚህ የፕሮጀክት ውጤቶች በፋከሊቲውና በመምህራን ተገቢው ድጋፍ ቢደረግላቸውና ተግባር ላይ ቢውሉ የተለያዩ ተግባራትን ለማቀላጠፍ አስተዋጿቸው ከፍተኛ መሆኑን የክበቡ ፕሬዝደንት ተማሪ አለማየሁ መገርሣ ገልጿል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ም/ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር አቶ ንጉሱ በቀለ ተማሪዎች በቴክኖሎጂ የታገዙ ሥራዎች  መሥራታቸው ያላቸውን እውቀትና ክህሎት ከማሳደግ በተጨማሪ ሀገሪቱ የምትፈልገውን በቴክኖሎጂ ብቁ የሆነ ዜጋ ከማፍራት አንፃር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

አውደ ርዕዩ ላይ የተገኙ አካላት ዝግጅቱ ማህበረሰቡ ስለ ኮሚፒውተር ሣይንስ፣ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ሶፍትዌር ምህንድስና የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው፣ አዲስና ዘመናዊ የፈጠራ ሥራዎችን የመመልከት ዕድል እንዲሁም የጥገናና ሌሎችም ድጋፎችን እንዲያገኝ የረዳ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

በዓውደ ርዕዩ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትና የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አመራሮች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች እና ሌሎችም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አካላት ተገኝተዋል፡፡