የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በውኃው ዘርፍ አራት የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞችን ለመክፈት ያስችለው ዘንድ ግንቦት 28/2010 ዓ/ም የውስጥ እንዲሁም ግንቦት 30/2010 ዓ/ም የውጭ የሥርዓተ ትምህርት ግምገማ አካሂዷል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የኢንስቲትዩቱ ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል የሥርዓተ ትምርት ግምገማው ፕሮግራሞቹን በራሳችን እና ከተለያዩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የምርምር ማዕከላት በተወጣጡ የዘርፉ ምሁራን በማስተቸት ዩኒቨርሲቲው በውኃ ዘርፍ ያለውን የዶክትሬት ፕሮግራም ቁጥር ለማሳደግ ይረዳል ብለዋል፡፡ የትምህርት ፕሮግራሞቹ በቀጣዩ የትምህርት ዘመን መከፈት የዩኒቨርሲቲውን በተለይም የኢንስቲትዩቱን የምርምር አቅም ከማጎልበት አኳያ ሚናቸው የጎላ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ም/ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር በሻ ሞገስ በበኩላቸው በምሁራኑ የተሰጡትን ማስተካከያዎችና ገንቢ ትችቶች  እንደ ግብዓት ተጠቅመን  በማካተት ፕሮግራሞቹ በቀጣይ ዓመት እንዲጀመሩ እናደርጋለን ብለዋል፡፡

የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር የቻለ ከበደ የሦስተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች በተለይ በውኃው መስክ መከፈታቸው  ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ያለውን ስምና ዝና ከማስቀጠል እና ሀገሪቱ በዘርፉ ያለባትን ከፍተኛ የባለሙያዎች እጥረት ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ሰዓት 4 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 10 የሁለተኛ ዲግሪ እና 1 የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞች ያሉት ሲሆን የጂኦኢንፎርማቲክስ ሥነ-ምድር ምልከታ ለሥነ-ውኃ ጥናት፣ የውኃ እና አካባቢ ምህንድስና፣ የውኃ ሀብት ምህንድስና እንዲሁም የከርሰ ምድር ውሃ ምህንድስና የሥርዓተ ትምህርት ግምገማው የተደረገባቸው አዲስ የፒኤችዲ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡