ለምስጉን መ/ራን፣ ርዕሳነ መ/ራንና ሱፐርቫይዘሮች በትምህርት ቤት ማሻሻል ላይ ያተኮረ ስልጠና ተሰጠ

የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ሣይንስ ትምህርት ቤት የማህበረሰብ አገልግሎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ከሚገኙ 7 የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለተወጣጡ 35  ምስጉን መ/ራን፣ ርዕሳነ መ/ራን እና ሱፐርቫይዘሮች በትምህርት ቤት መሻሻል፣ በአሳታፊ የማስተማር ስነ- ዘዴና በተከታታይ ሙያ ዕድገት ማሻሻያ ፕሮግራም /ሲፒዲ/ እንዲሁም  በችግር ፈቺ ምርምሮች ላይ ከሰኔ 7/2010 ዓ/ም  ጀምሮ ለ2  ቀናት ስልጠና ሰጥቷል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የማስተባበሪያ ጽ/ቤቱ ኃላፊ መ/ር ይሁንሰላም አስራት የስልጠናውን ዓላማ አስመልክተው እንደገለፁት በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ የሚታዩትን ከትምህርት ቤት ማሻሻል ፕሮግራም ጋር እንዲሁም ከመማር ማስተማር ሂደት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ክፍተቶችን መሙላት በተጨማሪም ልምድ ያላቸው መምህራን በት/ቤት ቆይታቸው ችግሮችን  በሣይንሳዊ መንገድ የሚፈቱበት እና አዲስ የሚመጡ መ/ራንን ተግባር ላይ የሚያበቁበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው ብለዋል፡፡

ትምህርት ህፃናትና ጎልማሶችን በመለወጥ በማህበረሰቡ ዘንድ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚያደርግ መሳሪያ መሆኑን በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ የገለፁት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ የመማር ትኩረት የማህበረሰቡን እሴቶች፣ ፍላጎቶችና ባህሪያት በልዩነትና በብዝሃነት አብሮ መኖርን ማስረፅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ከዚህም አንፃር ትምህርት የተፈለገውን ለውጥ ለማምጣት እንዲያስችል የትምህርት ጥራት ርዕሰ ጉዳይ ሊሆን የሚገባና ውጤታማነቱን ለማሳካት የሙያ ላይ ስልጠና አንዱና መሰረታዊ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ረገድ ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት በኩል ለትምህርት ሴክተር የትምህርት ጥራትን በማመላከት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የትምህርት ቤት ማሻሻያና አተገባበርን አስመልክቶ ጥሩ ዜጋ ለመፍጠርና ፍትሃዊ የሆነ ህብረተሰብን በቀጣይ ለማግኘት ት/ቤቶች መሻሻል አለባቸው ያሉት የስነ-ትምህርትና ስነ-ባህርይ ትምህርት ክፍል መ/ር ዶ/ር ድጋፌ ዳርዛ ትምህርት ቤት እንዲሻሻል የመምህራን አቅም፣ የትምህር ቤቱ እና የህብረተሰቡ ግንኙነት፣ የወላጆች ተሳትፎ መሻሻል እንዲሁም መልካም አስተዳደር መስፈን እና አስፈላጊ ግብአቶች መሟላት እንዳለባቸው በስልጠናው ወቅት ተናግረዋል፡፡ በአጠቃላይ የትምህርት ቤት መሻሻል የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ይጠይቃልም ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የሳይኮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መ/ር ወልደአብ ዳንኤል አሳታፊ የማስተማሪያ ስነ-ዘዴ ተማሪ ተኮር የሆነ፣ ከተመደበው ክፍለ ጊዜ አብዛኛውን ሰዓት ተማሪዎች በተሰጣቸው ርዕሰ ጉዳይ ላይ በስፋት የሚወያዩበትና መልስ የሚሰጡበት ሂደት ሲሆን መ/ሩ መንገድ የሚያሳይበትና መልሶ ምገባ የሚሰጥበት ሂደት ነው፡፡  ዘዴውም ተማሪዎች የማሰብ፣ የመመራመር፣ የማስታወስ፣ በራስ የመተማመን፣ የተግባቦትና የመሪነት ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ ብሎም  የእርስ በርስ ቅርርብ እንዲፈጥሩ ይረዳቸዋል ብለዋል፡፡  በመሆኑም ይህንን ሂደት መ/ራን በክፍል ውስጥ ተግባራዊ እንዲያደርጉት አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም በስልጠናው በተከታይ ሙያ እድገት ማሻሻያ /ሲፒዲ/ እና ችግር ፈቺ የምርምር አተገባበር እንዲሁም Instructional Planning and Implementation ላይ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡

ስልጠናው ተማሪዎችን በቡድን የሚያስተምሩበትን ዘዴ ግንዛቤ ያገኙበት፣ የመደገፍና የመከታተል አቅማቸውን የሚያሳድግ፣ የእርስ በእርስ ግንኙነት እንዲጠናከር እንዲሁም በየትምህርት ቤቱ ላሉ ችግሮች የጋራ ኃላፊነት እንዲወስዱና በጋራ የመፍታት ባህልንም እንዲያዳብሩ የሚያስችል አቅም የፈጠረላቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም የትምህርት ቤት ማሻሻያ ፕሮግራም የርዕሰ መምህር ወይም የአንድ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም በመሆኑ መሳተፍ እንደሚገባ ገልፀው ዩኒቨርሲቲው ስልጠናውን በማመቻቸትና  አስፈላጊውን ግብዓት በማሟላት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከቱ አመስግነዋል፡፡