የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል የባህል፣ የአኗኗር እና የአካባቢ ዓመታዊ የምርምር ዓውደ ጥናት ሰኔ 16/2010 ዓ/ም በጂንካ ከተማ አካሂዷል፡፡ በዓውደ ጥናቱ በደቡብ ኦሞ ዞን 16 ብሄሮች ባህል፣ አኗኗር እና አካባቢ ላይ ትኩረት ያደረጉ አምስት የምርምር ሥራዎች ቀርበው በዘርፉ ምሁራንና ባለድርሻ አካላት ተተችተዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የምርምር ማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ተመቸኝ ጉቱ እንደተናገሩት በአካባቢው በተሠሩ ምርምሮች ላይ የጋራ ውይይት በማድረግ በሚገኘው ግብዓት የምርምር ሥራዎቹ ወደ ኅብረተሰቡ ወርደው ችግሮችን እንዲፈቱ ማስቻል ዓውደ ጥናቱ ያስፈለገበት ዋና ዓላማ ነው፡፡ በዓውደ ጥናቱ የሚነሱ ሃሳቦች ማዕከሉ የተመሰረተበትን ግብ እንዲመታ ከማድረግ አኳያም ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በበኩላቸው ዓውደ ጥናቱ የዩኒቨርሲቲውን ብሎም የምርምር ማዕከሉን ተልዕኮ ከማሳካት አንፃር የጎላ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ገልፀው የምርምር ሥራዎቹ መድረክ ላይ ሳይወሰኑ ኅብረተሰቡን መጥቀም እና የመንግስትን የፖሊሲ አቅጣጫ ማመላከት መቻል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉ የዞኑን መንግስትና ማኅበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ የምርምር ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል ያሉት የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አለማየሁ ባውዴ የዞኑ አስተዳደር የምርምር ማዕከሉ የኅብረተሰቡን አኗኗር ለመቀየርና ለማሻሻል በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ ከጎኑ በመቆም የበኩሉን ሚና ይወጣል ሲሉ ቃል ገብተዋል ፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ገብሬ ኢንቲሶ የምርምር ማዕከሉ በእግሩ እንዲቆም አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳበረከተ ገልፀው ማዕከሉ በደቡብ ኦሞ ያለውን የባህልና ሥነ-ህይወት ብዝሃነት በማጥናት የዞኑ ማኅበረሰብ ኑሮ እንዲሻሻል ከማድረግ አንፃር ሚናው የጎላ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በአውደ ጥናቱ ከቀረቡ የምርምር ሥራዎች መካከል ‹‹pastoralism in Ethiopia: Policy Frameworks and Future Scenarios›› በሚል ርዕስ በመ/ር መለሠ ተሾመ የቀረበው ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ጥናት ተመራማሪው በአርብቶ አደሮች ህይወትና አኗኗር አሁን ላይ ያሉ ፈተናዎችንና ተግዳሮቶችን በመጥቀስ ለወደፊቱ ህይወታቸው መሻሻልና ለውጥ የሚረዱ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማመላከት ሞክረዋል፡፡ አርብቶ አደሮች በህግ አውጪው አካል ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑ፣ የውሃና ማህበራዊ አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ ተደራሽ አለመሆናቸው፣ ድርቅ፣ በየጊዜው በከብቶች ላይ የሚከሰቱ በሽታዎች እንዲሁም ግጭቶች በጥናቱ እንደ ተግዳሮት የተነሱ ችግሮች ናቸው፡፡ በጥናቱ የአርብቶ አደሩ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው ከሀገር ውስጥ ገበያ አልፈው ወደ ውጪ ገበያ መላክ ቢችሉ፣ አርብቶ አደሮች በአንድ ቦታ ተረጋግተው የሚኖሩበት ሆኔታ ቢመቻች እንዲሁም አርብቶ አደሮቹ ሌሎች አማራጭ የሥራ መሥኮችና የገቢ ማግኛ ዘዴዎች ቢሰማሩ የአርብቶ አደሮችን ሕይወት ማሻሻልና መቀየር እንደሚቻል ተጠቅሷል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የአርባ ምንጭና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅና የት/ት ቤት ዲኖች፣ የዘርፉ ተመራማሪዎች፣ መምህራን እንዲሁም የደቡብ ኦሞ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና ከዞኑ ወረዳዎች የተወጣጡ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡