ዩኒቨርሲቲው ለ31ኛ ጊዜ ተማሪዎችን በደማቅ ሁኔታ አስመረቀ

ዩኒቨርሲቲው በሁለት ት/ቤት፣ በሁለት ኢንስቲትዩትና በስድስት ኮሌጆች በ52 የቅድመ ምረቃ እና በ49 የድህረ ምረቃ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 5,965 ተማሪዎች ሰኔ 23/2010 ዓ.ም በአባያ ካምፓስ በሚገኘው አዳራሽ በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 4,181 ተማሪዎች ወንዶች ሲሆኑ 1,784 ተማሪዎች ሴቶች ናቸው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በ1979 ዓ.ም በውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ደረጃ ተቋቁሞ በ1996 ዓ.ም ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ በማደግ አሁን ላይ 6 ካምፓሶችን  መሥርቶ በ74 የቅድመ ምረቃ፣ በ83 የድህረ ምረቃና በ13 የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራሞች በአጠቃላይ ከ35 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ በማታ፣ በተከታታይና በርቀት መርሃ ግብሮች በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ያብራሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ተቋሙ ወደ ዩኒቨርሲቲ ደረጃ ካደገበት ጊዜ ጀምሮ በልዩ ልዩ መስኮች 48,365 ምሩቃንን በማፍራት ለሀገሪቱ የሰው ኃይል ሀብት ልማት አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

ተመራቂዎች የከፍተኛ ትምህርት ፕሮግራም በስኬት በማጠናቀቅ ከዩኒቨርሲቲው በገበዩትና ባካበቱት ዕውቀት፣ ክህሎትና መልካም አስተሳሰብ ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉ መንግስትና ህዝብ የሀገራችንን እድገት ለማቀላጠፍ እያደረገ ባለው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርከት ሊነሳሱ ይገባል ያሉት ፕሬዝደንቱ ተመራቂዎች ዩኒቨርሲቲውን ከመልቀቃቸው በፊት በሰጡት የግል አድራሻ መሰረት ከዩኒቨርሲቲው ጋር የማይቋረጥ ግንኙነት እንዲያደርጉና የአድራሻ ለውጥ ሲያደርጉም በዩኒቨርሲቲው ለሚመለከተው አካል መረጃውን እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የውኃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ሚኒስትር ዴኤታ፣ የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ሰብሳቢና የእለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የቀሰሙትን ዕውቀት ለሀገርና ለቤተሰብ በሚጠቅም መንገድ በሥራ ላይ በማዋል ሀገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ጉዞ በዘላቂነት የማስቀጠል አደራ እንደተጣለባቸው ገልጸዋል፡፡ አክለውም መንግስት ለወጣት ተመራቂዎች በተለያዩ ማዕቀፎች የበጀት ድጋፍ በማድረግ ባዘጋጀው የሥራ ዕድል  ተመራቂዎች ባለማመንታት በንቃት በመሳተፍ ራሳቸውን ውጤታማ እንዲያደርጉ፣ ሥራን ሳይንቁ በቁርጠኝነት እንዲሰሩና ችግር ከገጠማቸው በጽናትና በሰከነ መንፈስ እንዲያልፉ አሳስበዋል፡፡

በዕለቱ ከየትምህርት ክፍላቸው 1ኛ ለወጡ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሽልማት፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ ምሩቃን የወርቅ ሜዳሊያ፣ ከኢንስቲትዩት፣ ከኮሌጅና ከት/ቤት 1ኛ ለወጡ ሴት ምሩቃን ልዩ ሽልማት፣ ከአጠቃላይ ሴት ምሩቃን መካከል ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበች ምሩቅ የአንገት ሐብል እንዲሁም  ከአጠቃላይ ምሩቃን መካከል ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገበች ምሩቅ የዋንጫ ሽልማት ተበርክቷል፡፡

ከግብርና፣ ቢዝነስና እሴት ሰንሰለት ሥራ አመራር ት/ክፍል አጠቃላይ ውጤት 3.98 በማስመዝገብ የ2010 ዓ.ም የዋንጫ ተሸላሚ የሆነችው ተማሪ ሰላማዊት ወልደሚካኤል በሰጠችው አስተያየት ለስኬት ለመብቃት ዓላማን ለይቶ ማቀድና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው ስትል ሌሎች ተመራቂዎች በበኩላቸው የትምህርት ዓለምን አጠናቀው መመረቃቸው እንዳስደሰታቸው ጠቅሰው በተመረቁበት ሙያ ህብረተሰቡን በትጋት እንደሚያገለግሉና የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በተገቢው መልኩ እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡