የሳውላ ካምፓስ በሶስት የትምህርት መስኮች ያሠለጠናቸውን 130 ተማሪዎች ሰኔ 24/2010 ዓ/ም ለመጀመሪያ ጊዜ  በደማቅ ሥነ-ሥርዓት በሳውላ ከተማ አስመርቋል፡፡ ከተማሪዎቹ መካከል 66ቱ ወንዶች ሲሆኑ 64ቱ ሴቶች ናቸው ፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር መንግስት ለከፍተኛ ትምህርት ተደራሽነትና ጥራት ትኩርት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው የሳውላ ካምፓስ መከፈትም የዚህ ሥራ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት በመጠቀም የራሳቸውን ብሎም የሀገራቸውን ህይወት ለመቀየር በትጋት እንዲሠሩ አሳስበው በቀጣይ ካምፓሱን ለመማር ማስተማር ሥራ ምቹ ለማድረግ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የውኃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ሚኒስቴር የመጠጥ ውኃና ሳኒቴሽን ሚኒስትር ዴኤታና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ነጋሽ ዋጌሾ የዛሬዎቹ ተመራቂዎችና የምረቃው ሥነ-ሥርዓት በካምፓሱ ታሪክ የመጀመርያ በመሆኑ ሁሌም በበጎ ሲነሳ የሚኖር ታሪክ ነው ብለዋል፡፡ ለተመራቂዎቹ ባስተላለፉት መልዕክትም ተመራቂዎች አሁን ላይ ሀገራችን የጀመረችውን አዲስ የሠላም፣ የልማት እና ኢትዮጵያዊ የመደመርና የአንድነት መንፈስ በመገንዘብ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡

ተመራቂዎች የዛሬ ሦስት ዓመት ይህንን ካምፓስ ሲቀላቀሉ እምብዛም ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ነበር ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሆኖም የሀገሪቱን አቅምና ነባራዊ ሁኔታ በውል በመረዳት እውቀትና ክህሎት መሸመትን ዋና ዓላማ በማድረግ  አቧራና ጭቃው ሳይበግራቸው ለዛሬው ድል በቅተዋልና ተመራቂዎቹ ላሳዩት የዓላማ ፅናት ምስግና ይገባችዋል ብለዋል፡፡ በቀጣይም ተመራቂዎቹ  በሚኖራቸው ህይወት ከስሜታዊነትና እና አጓጉል ሱሶች ራሳቸውን በመጠበቅ በተማሩበት የሙያ መስክ በግልና በመንግስት በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች በመሰማራትና ውጤታማ በመሆን የቤተሰብና የሀገር ኩራት ለመሆን  በትጋት ሊሰሩ እንደሚገባ አጽኖት ሰጥተዋል፡፡

ከካምፓሱ ተመራቂ ተማሪዎች መካከል 3.95 በማምጣት የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚ የሆነው ተማሪ ብዙነህ ንጉሴ በሰጠው አስተያየት በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ያገኘውን እውቀትና ክህሎት በመጠቀም በተመረቀበት የት/ት መስክ ህብረተሰቡን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡

ሌላዋ ከካምፓሱ ሴት ተማሪዎች መካከል 3.94 በማምጣት የዕለቱ ልዩ ተሸላሚ የሆነችው በለጡ ከፈለኝ በሰጠቸው አስተያየት በሀገራችን ያለው የፋይናነስ ዘርፍ በርካታ ብልሹ አሰራሮችና ሌብነት የተንሰራፋበት መሆኑን ገልፃ በዘርፉ የሚታየውን ብልሹ አሰራርና ሌብነት ለመቀነስ የበኩሌን ሚና እወጣለሁ ብላለች፡፡

የሳውላ ካምፓስ በ2008 ዓ/ም የማስተማር ሥራውን የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በመደበኛ 1,003 እና በተከታታይ ትምህርት 138 በአጠቃላይ 1,141 ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስኮች እያሠለጠነ ይገኛል፡፡ ካምፓሱ በቀጣይ ዓመት በመደበኛው ፕሮግራም በቅድመ ምረቃ 500 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማሠልጠን እንዲሁም ሦስት የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራሞችን ከፍቶ ሥራ ለመጀመር ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡