‹‹ዩኒቨርሲቲው ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረውን መልካም ግንኙነትና ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል›› ዶ/ር ስምኦን ሽብሩ

አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ድጋፎችን እያደረገለት መሆኑን ጂንካ ዩኒቨርሲቲ ገልጿል፡፡ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ገብሬ ኢንቲሶ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲያቸው ዘንድሮ የማስተማር ሥራ የጀመረ ሲሆን ተቋሙ አዲስ እንደመሆኑ በርካታ ጉድለቶች እንዳሉበትና ጉድለቶችን ለመቅርፍ ዩኒቨርሲቲው ባቀረበው ጥያቄ መሰረት በአቅራቢያቸው የሚገኘው አንጋፋው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በርካታ ድጋፎችን እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

እንደ ፕሬዝደንቱ ማብራሪያ የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፎችን ጨምሮ ለአካዳሚክና አስተዳደር ሠራተኞች የተለያዩ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችን በመሥጠት እንዲሁም ለልምድ ልውውጥ ከዩኒቨርሲቲው ለሚላኩ ሠራተኞች ተገቢውን ልምድ በማካፈል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዩኒቨርሲቲያቸው የቤተ ሙከራ አገልግሎት እንዳልተጀመረ የገለፁት ፕሬዝደንቱ በዚህም ረገድ ተማሪዎችን ወደ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በመላክ በክፍል ውስጥ በንድፈ ሀሣብ ደረጃ የተማሩትን በተግባር እንዲፈትሹ ዩኒቨርሲቲው እየረዳቸው መሆኑን ፕሮፌሰሩ ገልፀዋል፡፡

የደቡብ ኦሞ ምርምር ማዕከል ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሲተዳደር እንደነበር ያስታወሱት ፕሬዝደንቱ ነገር ግን ማዕከሉ ከዩኒቨርሲቲው ባለው ርቀት ምክንያት ውጤታማ መሆን ባለመቻሉ በእሳቸው ፕሮፖዛል አቅራቢነት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥር እንዲተዳደር መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ማዕከሉ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥር መተዳደር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በርካታ የተሻሉና የማዕከሉን ግብ ሊያሳኩ የሚችሉ ውጤታማ የምርምር ሥራዎችን ሲሰራ ቆይቷልም ብለዋል፡፡

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተ በኋላ አንዳንድ ግለሰቦች የምርምር ማዕከሉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አካል እንዲሆን ጥያቄ እንደሚያነሱ የተናገሩት ፕሬዝደንቱ በግላቸው አሁን ላይ የምርምር ማዕከሉ በጥሩ እጅ ላይ እንደሚገኝ የሚያምኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሂደት ግን ጂንካ ዩኒቨርሲቲ አቅሙ እየጎለበተና እያደገ ሲመጣ ለማዕከሉ ካለው ቅርበት አንፃር በመወያየት ማዕከሉ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አካል ይሆናል ብለዋል፡፡

ጊዜው የመደመርና በጋራ የመሥራት መሆኑን ያወሱት የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር ስምዖን ሽብሩ በህዝቦች መካከል እየታየ ያለው የአንድነትና በጋራ የመሥራት መንፈስ በተቋማት መካከል ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ዩኒቨርሲቲው ከጂንካ ዩኒቨርሲቲ ጋር የጀመረውን መልካም ግንኙነትና ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የምርምር ማዕከሉን የወደፊት እጣ ፈንታ በተመለከተ ሃሳባቸውን የሰጡት ም/ፕሬዝደንቱ አሁን ላይ የምርምር ማዕከሉ በአ/ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሥር ነው ማለት ጂንካ ዩኒቨርሲቲን የምርምር ማዕከሉ ጉዳይ አይመለከተውም ማለት እንዳልሆነ ተናግረው በሂደት ዝግጅት በማድረግ የምርምር ማዕከሉ ወደ ጂንካ ዩኒቨርሲቲ የሚዞርበት ሁኔታ የሚመቻች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ጂንካ ዩኒቨርሲቲ በ2010 የትምህርት ዘመን የማስተማር ሥራውን የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በ4 ኮሌጆችና በ14 ትምህርት ክፍሎች 1,094 ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡