የመላ ኢትዮጵያ ውኃ ዋና ስፖርት ሻምፒዮና በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተካሄደ

የመላ ኢትዮጵያ የውኃ ዋና ስፖርት ሻምፒዮና ከሰኔ 26-29/2010 ዓ.ም ለ4 ተከታታይ ቀናት በዩኒቨርሲቲው ተካሂዷል፡፡ በውድድሩ የአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልሎችና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተካፋይ ሆነዋል፡፡ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በውድድሩ ከ180 በላይ የውኃ ዋና ስፖርተኞች ተካፋይ ሲሆኑ ውድድሩ ድብልቅ ቅብብል፣ ቢራ ቢሮ፣ ነጻ ቀዘፋ፣ የግል ድብልቅ፣ ደረት ቀዘፋ፣ የጀርባ ቀዘፋና ሌሎች የውኃ ዋና ስፖርት ዓይነቶችን አካቷል፡፡

የኢትዮጵያ ውኃ ዋና ፌዴሬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቀልቤሳ ኤባ በንግግራቸው ይህ ስፖርት ከ2 ዓመታት መቋረጥ በኋላ እንዲካሄድ ላስቻሉ የስፖርት አካላት አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ ውድድሩ በተለይ ሀገርን ሊወክሉ የሚችሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ተፎካካሪ የውኃ ዋና ስፖርተኞችን ለማፍራት ዕድል የሚፈጥር ብሎም ስፖርተኞች ልምድና ተሞክሯቸውን እንዲለዋወጡ ከፍተኛውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አቶ ቀልቤሳ ተናግረዋል፡፡

በውድድሩ በሁለቱም ጾታዎች ደቡብ 16 ወርቅ፣ ኦሮሚያ 5 ወርቅ እና አማራ 2 ወርቅ አግኝተዋል፡፡ ኦሮሚያ 13፣ ደቡብ 7፣ እንዲሁም አማራ 3 የብር ሜዳሊያዎች ያገኙ ሲሆን ደቡብ 8፣ አማራና ኦሮሚያ ስድስት ስድስት የነሀስ ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል፡፡ በአጠቃላይ ውጤት በወንዶች ደቡብ እና በሴቶች ኦሮሚያ አሸናፊ ሲሆኑ አማራና አዲስ አበባ ከተማ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

በውድድሩ አሸናፊ የሆኑ ስፖርተኞች ከየክልሉ የውኃ ዋና ቡድን መሪዎች የሜዳልያ ሽልማት ሲቀበሉ በአጠቃላይ በወንዶች ደቡብ፣ በሴቶች ኦሮሚያ የተዘጋጀላቸውን የዋንጫ ሽልማት የዕለቱ የክብር እንግዳ ከሆኑት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ፕሮግራም ግምገማና ትግበራ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ከዶ/ር ንጉሴ ባደገ እጅ ተቀብለዋል፡፡

በመጨረሻም በውድድሩ ለተሳተፉ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች፣ ዳኞች፣ የቡድን መሪዎች እንዲሁም ውድድሩ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድጋፍ ላደረጉ አካላት የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡