በ2010 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አተገባበር ላይ ውይይት ተደረገ

ዩኒቨርሲቲው በሥሩ ከሚገኙ ፕሬዝደንቶችና የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች ጋር በ2011 በጀት ዓመት ዕቅድ አተገባበር ላይ ነሐሴ 2/2010 ዓ/ም ውይይት አድርጓል፡፡ በውይይቱ የ2010 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀሞን በመገምገም የተመዘገቡትን ጠንካራ ጎኖች በማጠናከር ብሎም ከታዩት ክፍተቶች በመማር ለቀጣዩ የተሻለ ሊሠራ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡

የስትራቴጂክ ዕ/ዝ/ት/ግ/ዳይሬክተር አቶ ገዝሙ ቀልቦ እንደገለፁት የውይይቱ ዓላማ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር፣ የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎች በተደራጀ ዕቅድ በመምራትና በመተግበር የትምህርት ጥራት፣ ተገቢነትና ፍትሃዊነትን ከማረጋገጥ አኳያ የሚታዩ ክፍተቶችን አርሞ ለተቋሙ የተሻለ ለውጥን ማምጣት ነው፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ወቅቱንና ሚዛናዊነትን የጠበቀ እና ሥራን መሠረት ያደረገ የውጤት ተኮር ሥርዓትን መከተል ብሎም የላቀ አፈፃፀም ያላቸውን መሸለምና ሊደገፉ የሚገባቸውን መደገፍ ለቀጣዩ የዕቅድ አተገባበር ስኬት ፋይዳው የጎላ በመሆኑ የቅርብ ኃላፊዎች ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ ይገባል ብለዋል፡፡

የትምህርት ፍትሃዊነትና ተደራሽነትን በማረጋገጥ እና አግባብነትና ጥራትን በማስጠበቅ፣ የመምህራንና ሰራተኞች አቅርቦትና ልማትን በማጠናከር፣ መሠረተ ልማትን በማሟላት፣ የማህበረሰብ አገልግሎትን በማስፋፋት፣ ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማጠናከር፣ በቡድን የመሥራት ችሎታን በማሳደግ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመለየትና የመፍቻ ስትራቴጂካዊ ዕቅድን ዘርግቶ በመተግበር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮችን በመለየትና የማክሰሚያ ስልቶችን በመቀየስ እንዲሁም የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃን በማሻሻል ረገድ በ2010 በጀት ዓመት የተሻሉ አፈፃፀሞች መመዝገባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡

የትምህርትና ቴክኖሎጂ ልማት ሠራዊት አደረጃጀትን ማጠናከር፣ በቅድመና ድህረ- ምረቃ ፕሮግራሞች የሴት ተማሪዎችን ቅበላ መጠን ማሳደግ፣ አገልግሎት አሠጣጥን ማሻሻል የካይዘንና ሚዛናዊ የውጤት ተኮር ሥርዓት መዘርጋት፣ የትምህርት ጥራትን በማሳደግ ውጤታማ አሰራርን መዘርጋት፣ እውቅና ባላቸው ጆርናሎች ላይ ለሚታተሙ የምርምር ውጤቶች ድጋፍ ማድረግ፣ ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የምርምር ሲምፖዚየሞችን ማካሄድ፣ በተለያዩ የምርምር ዘገባዎች ማህበረሰቡን ያሳተፈ ውይይት ማካሄድ፣ ችግር ፈቺ  ምርምሮችን በማህበረሰቡ ቋንቋ ማከናወን፣ ቋሚ የሴት ተመራማሪዎችን ቁጥር ማሳደግ እንዲሁም የዩኒቨርሲቲ ኢንደስትሪ ትስስርን ማጠናከር በ2011 በጀት ዓመት ትኩረት ተሰጥቶባቸው ከሚከናወኑት ተግባራት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

በዩኒቨርሲቲው ለ2011 በጀት ዓመት ከተመደበው 902,980,000 ብር መደበኛ በጀት ውስጥ 34,032,500 ብር ለማማከርና ማህበረሰብ አገልግሎት፣ 24,203,100 ብር ለጥናትና ምርምር፣ 127,670,600 ብር ለተማሪዎች አገልግሎት፣ 466,531,200 ብር ለመማር ማስተማር እና ቀሪው 250,542,600 ብር ለአስተዳደር ዘርፍ የሥራ ማስኬጃ የሚውል ይሆናል፡፡