‹‹ኢንስቲትዩቱ በ2011 የትምህርት ዘመን በትምህርት ጥራትና የአካባቢውን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን መሥራት ላይ ትኩረት ያደርጋል›› ዶ/ር አብደላ ከማል

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መሠረት የሆነው የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ2011 በጀት ዓመት ከመደበኛው የመማር ማስተማር ሥራ ባሻገር የአካባቢውን ማህበረሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርጉና የውሃ ሃብት አጠቃቀምን የሚያሻሽሉ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ እንደሚሰራ ገለፀ፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አብደላ ከማል ኢንስቲትዩቱ በ2010 ዓ/ም እንደገና መቋቋሙን አስታውሰው እንደ መጀመሪያ ዓመት ከመማር ማስተማር ሥራ ባሻገር የኢንስቲትዩቱን መዋቅር የማደራጀት እና የሰው ኃይልና ግብአት የማሟላት ሥራዎችን ሲሰራ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡ ኢንስቲትዩቱ ተቋሙን ከመሰል አገር አቀፍና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር የማስተዋወቅ ሥራዎችን እየሰራ ሲሆን ከመሰል ተቋማት ጋር በመማር ማስተማርና በምርምር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነቶችን መፈራረሙን እንዲሁም በቅርቡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቀረበ ጥያቄ መሠረት ቻይና ከሚገኝና በውሃው ዘርፍ አንጋፋ ከሆነ ዩኒቨርሲቲ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ለመፈራረም ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በዚህ ዓመት ኢንስቲትዩቱ ነባርና አዲስ  ተማሪዎችን ለመቀበል እንዲሁም 4 አዲስ የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞችን ከፍቶ ሥራ ለመጀመር ቅድመ ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን የተናገሩት ዶ/ር አብደላ የተማሪዎችን መማሪያ ክፍሎች፣ ማደሪያ ህንፃዎች፣ የመብራትና የውሃ መስመሮች የመጠገንና የማደስ ሥራዎች በአግባቡ ተሰርተው እየተጠናቀቁ ነው ብለዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በዚህ የዝግጅት ምዕራፍ የኮርሶች ድልድል ተሠርቶና ሁሉም መምህራን ዝግጁ ሆነው የተማሪዎችን መግባት ብቻ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በያዝነው ዓመት ተማሪዎቻችን ለመጀመሪያ ጊዜ የመውጫ ፈተና ይወስዳሉ ያሉት ዶ/ር አብደላ ተማሪዎች ፈተናውን በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ኢንስቲትዩቱ ስትራቴጂዎችን ቀይሶ እየሰራ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር አብደላ እንደገሉት ከዚህም በተጨማሪ የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንፃር ለተግባር ትምህርት ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት በመስጠት በየፋካልቲው ያሉትን ቤተ- ሙከራዎችና የተግባር መለማመጃ ወርክሾፖች በግብአት የማሟላትና ለተግባር ልምምድ ምቹ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ ይገኛል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተልዕኮዎች መካከል ምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ዋነኞቹ መሆናቸውን የጠቀሱት ዶ/ር አብደላ ኢንስቲትዩቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ቀርፆ ይሠራልም ብለዋል፡፡ ለአብነትም በዩኒቨርሲቲው ሙሉ ወጪ የሻራ ቀበሌ ማህበረሰብን የንፁህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ የሚያደርግ ትልቅ ፕሮጀክት በዚህ ዓመት ለመሥራት ታቅዶ ሥራውን ለማስጀመር ኢንስቲትዩቱ እንቀስቃሴ መጀመሩን ገልፀዋል፡፡ ሣ/ዳይሬክተሩ አክለው እንደተናገሩት ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ የሀገርና ውስጥ የውጭ ሀገር ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመሆን ህብረተሰቡን የንፁህ መጠጥ ውሃ  ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶችን ለመሥራት በዕቅድ ይዟል፡፡

ከምርምር ጋር ተያይዞ በኢንስቲትዩቱ ሥር የሚገኘውን የውሃ ሃብት ምርምር ማዕከል ለማጠናከር እየተሠራ መሆኑንና  በቅርቡ የምርምር ማዕከሉ የራሱን ህንፃ መረከቡን እንዲሁም በአጭር ጊዜ ውስጥ የማዕከሉን ቤተ-ሙከራ በማደራጀት ከንፁህ መጠጥ ውሃ፣ ከመስኖ ውሃ አጠቃቀም እና በአካባቢው የሚገኙ የውሃ ሃብቶች ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ትልልቅ የምርምር ሥራዎችና ፕሮጀክቶች እንደሚሰሩ ዶ/ር አብደላ ተናግረዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከዚህ ቀደም በውሃው ዘርፍ በሀገር አቀፍም ሆነ በአህጉር ደረጃ ታዋቂና አንጋፋ እንደነበር የተናገሩት ዶ/ር አብደላ አሁን ላይ ይህ እውቅና በተወሰነ ደረጃ መደብዘዙን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም ከቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሥር እንዲሆን መደረጉ አንዱ ምክንያት መሆኑን ተናግረው በአሁኑ ሰዓት ኢንስቲትዩቱ ራሱን ችሎ እንደገና በመቋቋሙ የቀድሞ ስምና ዝናውን ለመመለስ ይሥራል ብለዋል፡፡

የውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ1979 ዓ/ም በቀድሞው የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማሪያም ተመርቆ የተከፈተ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት 4 የመጀመሪያ ፣ 9 የሁለተኛ እና 5 የዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራሞች አሉት፡፡