በአገራዊ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ውጤት ላይ በዩኒቨርሲቲው ከመስከረም 28/2011 ዓ/ም ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ የቆየው የግብዓት ማሰባሰብ የመምህራንና የሰራተኞች የውይይት መድረክ ተጠናቀቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ እንደገለጹት የውይይት መድረኩ በአገር አቀፍ ደረጃ ለመተግበር በትምህርት ሚኒስቴርና በሌሎችም አጋር አካላት እየተሰራ ባለው የትምህርትና የሥልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ውጤት ላይ በተዘጋጁ  ሰነዶች ላይ ጥልቅ ውይይት በማድረግ ግንዛቤ ለመፍጠርና የሀሳብ ግብዓት ለመሰብሰብ ታልሞ የተዘጋጀ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ እንደ አገር የተቀመሩ ዘላቂ የልማት ግቦችን ከትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው ጋር በማስተሳሰር ለትምህርት ልማት ግቦች መሳካት የበኩሉን እንዲወጣ የመድረኩ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር ዳምጠው አክለዋል፡፡

በአጠቃላይ በሁሉም ካምፓሶች በነበሩ መድረኮች በአገራዊ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ጥናት ውጤት ላይ ያተኮሩ ስድስት የመወያያ ሰነዶች ቀርበዋል፡፡ ሰነዶቹ በዋናነት የኢትዮጵያ ትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ታሪካዊ ዳራ፣ የከፍተኛ ትምህርት ችግሮችና የመፍትሄ ሃሳቦች፣ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ አመራርና አስተዳደር የሪፎርም ሃሳቦች፣ የአጠቃላይ ት/ት ፍኖተ ካርታ፣ በቴ/ሙ/ት/ሥ ዘርፍ የለውጥ ምክረ ሃሳቦች እንዲሁም የት/ትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ ለዘላቂ ልማት ግቦች ስኬት ላይ ትኩረት ያደረጉ ናቸው፡፡

የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲውን ወቅቱ በሚፈልገው አግባብ በጥልቀት መቃኘትና መተግበር ለሰው ኃይል እምቅ አቅም መጎልበት ከሚያበረክተው ጥቅም ጎን ለጎን የአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦችን ኑሮ ለማሳደግ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

በዚህም አገሪቱ በ1986 ዓ.ም የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ የቀረፀች ሲሆን ሰብአዊ ሀብትን በማልማት ሀገሪቱን በአጭር ጊዜ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ብሎም ሩቅ ባልሆነ ጊዜ ከበለፀጉት ኃያላን አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሠረታዊ መሆኑን በመረዳት ለመስኩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል፡፡

የተቀመጠውን ዓላማና ግብ ለማሳካት ባለፉት 24 አመታት የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራት ለማጐልበት ሰፊ ሥራዎች መሰራታቸውን የሚያሳዩ ዝርዝር ተግባራት የቀረቡ ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ በትምህርትና ሥልጠና የሚያልፈው ትውልድ ከትምህርትና ሥልጠናው እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት አንጻር፣ የኩረጃና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር፣ በትምህርትና ሥልጠና ዘርፎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶና ተናቦ ከመሥራት አንጻር፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሥራ በአግባቡ ያልጎለበተና ኢኮኖሚውን በሚፈለገው መጠን እያገዘ አለመሆን እንዲሁም ሌሎች ሰፊ ጉድለቶች እንዳሉ እና ከሌሎች አገራት ጋር ሲነፃፀር የትምህርትና ሥልጠና ጥራታችን በዝቅተኛ ደረጃ መሆኑም ተገልጿል፡፡

ተሳታፊዎች ሰነዱን መነሻ በማድረግ በቡድን ተወያይተውባቸው የመፍትሄ ሃሳቦችን አቅርበዋል፡፡ የፍኖተ ካርታው ጥናት ላይ በተለይም ከሀገራዊ የልማት አቅጣጫዎች ጋር በማስተሳሰር ለመተግበር መሞከሩ መልካም መሆኑን ገልጸው መሻሻል ባለባቸው ውስን ጉዳዮችና የስያሜ አሰጣጥ ላይ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በኃይል መድረክ ውይይት ቀርቦ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡ በተጨማሪም ፖለቲካዊ አደረጃጀቶች በትምህርት ተቋማት እንዳይተገበሩ እና ተጨባጭ የሆነ የአካዳሚክ ነፃነት እንዲተገበር የሚሉ ሃሳቦች በሁሉም ውይይቶች በአንክሮ ከተነሱት መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ነው፡፡

መንግስት ይህን መሰል የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ በማዘጋጀት እና በአገራችን ባልተለመደ መልኩ ሁሉንም አሳታፊ በማድረግ ማስተቸት መቻሉን በማድነቅ በፍጥነት ወደ ተግባር እንዲገባ ጠይቀው  ለስኬቱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንትና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች ቀደም ሲል በሰነዱ ዙሪያ ትምህርት ሚኒስቴር አዘጋጅቶ የተካፈሉበትን የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሠረት በማድረግ ሳውላን ጨምሮ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች የውይይት መድረኮቹን መርተዋል፡፡

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በ2010 ዓ/ም የበጀት ዕቅድ አፈፃፀም እና በ2011 ዓ/ም ዕቅድ ላይ ተወያይቶ የጋራ መግባባት በመፍጠር ውይይቱ ተጠናቋል፡፡ ለሦስት ተከታታይ ቀናት በነበረው የውይይት መድረክ በሁሉም የዩኒቨርሲቲው ካምፓሶች የሚገኙ ከ1600 በላይ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች የየዘርፉ ኃላፊዎችና አስተባባሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት