ባለፈው በጀት ዓመት በሥነ-ምግባርና በፀረ-ሙስና ትግሉ የታዩ ክፍተቶችን በማረምና ጠንካራ አፈፃፀሞች ላይ ትኩረት በማድረግ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ገለፀ፡፡

የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘውዱ ዳባ እንደገለፁት በሙስና ትግሉ ላይ ቁርጠኛ እንዳንሆን የሚያደርጉ ምክንያቶችን በመለየት ሁሉም የባለቤትነት ስሜት አድሮበት በፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ የበኩሉን ሚና እንዲጫወት ለማስቻል ትግሉን ማጠናከር አስፈልጓል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ ከባለድሻ አካላት ጋር በመሆን ባደረገው ማጣራት በ2010 በጀት ዓመት  ከቀረቡ 55 ጥቆማዎች 32ቱ ተገቢውን ህጋዊ ውሳኔ ያገኙ ሲሆን ቀሪዎቹ 18 ጥቆማዎች ውሳኔያቸው በሂደት ላይ ነው፡፡ በ2011 በጀት ዓመት 1ኛው ሩብ ዓመት ከቀረቡ 9 ጥቆማዎች 8ቱ ጉዳያቸው ተጣርቶ ወደ በላይ አካል መመራቱን አቶ ዘውዱ ገልፀዋል፡፡

የሚቀርቡ አንዳንድ ጥቆማዎች መሠረተ-ቢስ መሆናቸው፣ በትግሉ ላይ በእኩል ደረጃ ጠንካራ አቋም ያለመኖር፣ ህገ-ወጥ ሠነዶችን ህጋዊ አድርጎ ለማቅረብ መሞከር እንዲሁም ተጣርተው በሚቀርቡ ጥፋተኛ አካላት ላይ የበላይ አመራሩ ወቅቱን የጠበቀና ጠንካራ ውሳኔ  ያለማስተላለፍ ችግር በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ትግሉ ላይ ከታዩ ክፍተቶች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

አቶ ዘውዱ እንደተናገሩት ዳይሬክቶሬቱ የአገልግሎት አሠጣጥ ስታንዳርድ አዘጋጅቶ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑ የሥራ ክፍሎችን በመለየት በእቅዶቻቸው ላይ በማካተት ትግሉን ማጠናከር እንዲችሉ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡

የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፣ ፋይናንስና በጀት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፣ ይዞታ ልማት ዳይሬክቶሬት፣ ግዥና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፣ ቢዝነስና ልማት ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት፣ ጠቅላላ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት እና ግንባታ ጽ/ቤት ለሙስና ተጋላጭ የሥራ ክፍሎች መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት