ዩኒቨርሲቲው በ2011 በጀት ዓመት በሁሉም ካምፓሶች የህፃናት ማዋያ ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆኑን የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ገለፀ፡፡ ዳይሬክቶሬቱ ማዕከላቱን በቅርበት እንዲከታተል ኃላፊነት የተሠጠው ሲሆን በያዝነው በጀት ዓመት የቢሮ መጠሪያውን ወደ ‹‹ሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት›› እንደሚቀይርም አስታውቋል፡፡

የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሠናይት ሳህለ እንደገለፁት በፌዴራል የመንግስት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/2010 አንቀፅ 48(6) መሠረት ሴት የመንግስት ሠራተኞች ከወሊድ በኋላ ወደ ሥራ ገበታቸው ሲመለሱ በሚሰሩበት ተቋም ውስጥ ህጻን ልጆቻቸውን በቅርበት እየተንከባከቡና እየተከታተሉ መደበኛ ሥራዎቻቸውን እንዲያከናውኑ ለማገዝ የህፃናት ማቆያ ማቋቋም አስፈላጊ ነው፡፡ በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ 36(1) መሠረት ህጻናት ከወላጆቻቸው ማግኘት የሚገባቸውን ተገቢውን እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው ይደነግጋል፡፡

የህፃናት ማቆያዎቹ መቋቋም ዓላማዎች ከሆኑት ውስጥ እናቶቻቸው በሥራ ምክንያት በአቅራቢያቸው ባለመኖራቸው ምክንያት በህፃናት ጤንነትና ደህንነት ላይ የሚደርሰውን አሉታዊ ተፅዕኖ መቀነስ፣ በመንግስት ተቋማት ውስጥ የተሰማሩ እናት ሠራተኞች በህጻን ልጆቻቸው ምክንያት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚፈጥሩትን ክፍተቶች መሙላት፣ በሴት ሠራተኞች ላይ የሚደርሱ ጫናዎችን መቀነስ እና ውጤታማነታቸውን ማሳደግ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

የህፃናት ማዋያዎቹ ከመደበኛው የሥራ መግቢያ ሰዓት  እስከ ሥራ መውጫ ሰዓት ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ሲሆን የመኝታ፣ የማረፊያ፣ የመጫወቻ፣ የምግብ ማብሰያ፣ የመመገቢያ አቅርቦትና አገልግሎት እንዲሁም የእንክብካቤ፣ የቅርብ ክትትል እና የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና አገልግሎቶችን አካቷል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ አገልግሎቱን ለማግኘት ወላጆች የማንነት መግለጫ መታወቂያ ማቅረብ የሚኖርባቸው ሲሆን የህፃናቱን ምግብ በተመለከተ ከማቆያ ማዕከሉ ጋር በሚደረግ ስምምነት ወላጆች አዘጋጅተው ማቅረብ አልያም ተመጣጣኝ ክፍያ ፈጽመው የማዕከሉን አቅርቦት መጠቀም ይችላሉ፡፡ የማዕከሉን የውስጥ ግብዓት ከማሟላት ጀምሮ ተንከባካቢ ሞግዚት የመቅጠሩ ተግባር የዩኒቨርሲቲው ይሆናል፡፡

ወ/ሪት ሠናይት እንደገለጹት በህፃናት ደህንነት ላይ የወጡትን ህግጋት መሠረት በማድረግ በህፃናት ጤንነት ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ኬሚካሎች፣ ብናኞች፣ ድምፅ ያላቸው የማምረቻ ቦታዎችና መሠል ጎጂ ነገሮች የራቀ የህፃናት ማቆያ ለመገንባት ዩኒቨርሲቲው የቦታ መረጣ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው፡፡ የህፃናት ማቆያ ማዕከላቱ ህንፃዎች የመኝታ፣ የመጫወቻና የንፅህና መጠበቂያ ክፍሎችን የሚያካትቱ ይሆናል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት