2011 በጀት ዓመት የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት የማህበረሰቡን የትምህርት፣ የባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የጤና እንዲሁም የአካባቢና ማህበራዊ ልማት ፍላጎቶችን የሚደግፉ አገልግሎቶችን በመስጠት ለአካባቢው ልማት እና ዕድገት እንደሚሰራ የዘርፉ ዳይሬክተር ገለፁ፡፤ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ እንደገለፁት ዳይሬክቶሬቱ ባለፈው በጀት ዓመት አብዛኛዎቹ ስራዎች በተያዘላቸው ዕቅድ መሠረት ያከናወነ ሲሆን ከነዚህም መካከል በነፃ የህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለ1339 አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎች የምክር፣ የክስ አቤቱታ ፅሁፍ እና ጥብቅና አገልግሎት የመስጠት በነባር የጎልማሶች ትምህርት ማዕከላት በደረጃ አንድ 255 ተማሪዎችን በማስተማር ወደ ደረጃ ሁለት ማሸጋገር እንዲሁም ከ96 የደረጃ ሁለት ተማሪዎች መካከል 37 ጎልማሶች ደረጃ ሁለትን ጨርሰዉ ዞናዊ 4ኛ ክፍል ፈተና ወሰደው ወደ 5ኛ ክፍል መዛወራቸውን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ዳይሬክቶሬቱ በአካባቢው ለሚገኙ የ2ኛ ደረጃ እና መሰናዶ ት/ቤት ለ105 መምህራን በሳይንስ፣ በICT እና በቋንቋ የአቅም ማጎልበቻ ሥልጠና መስጠቱ ፣ ለአርባ ምንጭ 2ኛደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የመማሪያ ህንጻ ግንባታ የሁለት ሚሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉ፣ 2010 .ም በSTEM Project በአጠቃላይ ትምህርት ከ7-12ኛ ክፍል ላሉ ከፍተኛ ውጤት ላመጡ ከጋሞ ጎፋ፣ ከሰገን ህዝቦችና ደቡብ ኦሞ ዞን ለተወጣጡ ለ230 ተማሪዎች በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሂሳብ ትምህርት ሥልጠና ለተማሪዎች መሰጠቱ በሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት አማካኝነት ለ5 ጤና ጣቢያዎችና ለአንድ ትምህርት ቤት የሶላር መብራት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን እና 3ኛዉ ዓመታዊ የማህበረሰብ ሳምንት “በተፈጠረው ዕድል ማህበረሰቡን እናገልግል“ በሚል መሪ ቃል በአውደ-ርዕይና በማህበረሰብ ውይይት በድምቀት መከበሩ በበጀት ዓመቱ በዳይሬክቶሬቱ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

2011 በጀት ዓመት ለማህበረሰብ አገልግሎት ዩኒቨርሲቲው ከ34 ሚሊየን ብር በላይ የመደበ መሆኑንና ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ8 ሚሊየን ብር በላይ ብልጫ እንዳለው የተናገሩት ዳይሬክተሩ በዘንድሮው በጀት ዓመት አዳዲስ የነፃ ህግ አገልግሎት መስጫ ማዕከላት፣የተቀናጀ ተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርት ማዕከላት እንደሚቋቋሙና በሳሃይ ሶላር ፕሮጀክት ተጨማሪ ጤና ጣቢያዎችንና ት/ቤቶችን የመብራት ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እንዲሁም ሌሎች ተጨማሪ ችግር ፈቺ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማከናወን እንደታቀደ ገልፀዋል ፡፡

ከተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ጋር በተያያዘም የቤሬ ተራራን መልሶ ለማልማት ዩኒቨርሲቲው በተረከበው 150.86 ሄክታር መሬት ላይ ከ4,600 በላይ ችግኞች ተተክለዉ ጥበቃና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ሲሆን በተራራው ላይ የአካላዊና ሥነ-ህይወታዊ ሥራ እየተሰራ እንደምገኝና ይህም ሥራ በያዝነው በጀት ዓመት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ዩኒቨርሲቲው እያስገነባ የሚገኘውን የማህበረሰብ ሬድዮ ጣቢያ ግንባታ ሥራውን በ2010 ዓመት 30 ከመቶ ለማድረስ ቢታቀድም ግንባታው ሙሉ በሙሉ የቆመ በመሆኑ የግንባታ ሥራውን ለማስቀጠል የሚመለከተው ሁሉ ክትትል እንዲያደርግ ጥር አቅርበዋል ፡፡ በ2011 በጀት ዓመት የግንባታውን አፈፃፃም ወደ 75% ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ዶ/ር ተክሉ ተናግረዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በዩንቨርሲቲው የተሰየመውን በተለምዶ ሳልባጅ ተራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውን አደባባይ ለማልማት በታቀደዉ መሠረት አሸናፊዉ ድርጅት ተለይቶ ዉል የመግባትና የሳይት ርክብክብም የተፈፀመ በመሆኑ እና ግንባታው በያዝነው የበጀት ዓመት እንደሚጠናቀቅም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በያዝነው በጀት ዓመት ባገባደድነው የመጀመርያ ሩብ ዓመት የታቀዱ ሥራዎች በአግባቡ የተከናወኑ ሲሆን ለሚመለከተው አካልም ርፖርት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

በመጨረሻም ዳይሬክቶሬቱ በዓመቱ ለመሥራት ያቀዳቸውን ተግባራት ሙሉ በሙሉ ለመፈፀም በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛልም ብለዋል፡፡