የዩኒቨርሲቲው ኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ከቦንኬ፣ ከካምባ ፣ ከደምባ ጎፋና ከዛላ ወረዳዎች ለተወጣጡ 80 ሞዴል ሴት አርሶ አደሮች በተሻሻለ የወተት መናጫ ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ  ከጥቅምት 15-16/2011 ዓ.ም ለሁለት ቀናት የቆየ ሥልጠና በሣውላ ካምፓስ እና በካምባ ከተማ ሰጥቷል፡፡ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  ዶ/ር ተክሉ ወጋየሁ ዩኒቨርሲቲው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ችግር ፈቺ የሆኑ ምርምሮችን በማካሄድ፣ የአካባቢውን ማህበረሰብ ችግር ለመፍታት የሚያስችሉ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በመፍጠር እንዲሁም ቴክኖሎጂዎችን ከህብረተሰቡ ጋር በማላመድ፣ ችግሮችን በመለየትና መፍትሄዎችን በመስጠት የህብረተሰቡን ኑሮ ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀው ይህም ሥልጠና አንዱ ማሳያ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ከአምራች ኢንደስትሪዎች ጋር በቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ዘርፈ ብዙ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑን የገለፁት  የኢንደስትሪ ትስስርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር ቶሌራ ሴዳ  የሥልጠናው ዓላማ   በወተት ምርት ግንባር ቀደም የሆኑ ሴቶችን በተሻሻለ የወተት መናጫ ዘዴ ጽንሰ ሃሳብና ተግባር ልምምድ ላይ ግንዛቤ  በማስጨበጥ ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ለራሳቸው ከመጠቀም አልፈው በአካባቢያቸው ለሚገኙ ሌሎች ወተት አምራች ሴት አርሶ አደሮች እንዲያካፍሉ በማድረግ የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ዳይሬክቶሬቱ በ2011 በጀት ዓመት  ወደ ህብረተሰቡ ለማሸጋገር  ካቀዳቸው 3 ቴክኖሎጂዎች መካከል  አንዱ የሆነው ይህ የተሻሻለ የወተት መናጫ ቴክኖሎጂ ምን ያህል የህብረተሰቡን ችግር እየፈታ እንደሆነ አፈፃፀሙን በመገምገም መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች በመለየት የማሻሻያ ሥራ ከየወረዳዎቹ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ጠቁመዋል፡፡

የደምባ ጎፋ ወረዳ ም/አስተዳዳሪና የወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ቸርነት ለበነ የወተት አምራቾች ከዚህ ቀደም  ልማዳዊና ኋላቀር አሰራር በመጠቀማቸው የምርት ብክነት ይፈጠር እንደ ነበር ገልፀው  ሠልጣኞች  ከሥልጠናው በሚያገኙት  ዕውቀት እና ክህሎት  ተጠቅመው የተሻለ ውጤት እንደሚያገኙና ተሞክሮዎችን ለሌሎች ያካፍላሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የካምባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደስታ ሳሊሌ በበኩላቸው መንግስት የተለያዩ ልማዳዊ አሰራሮችን በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ለማድረግ  እየሰራ ባለበት ወቅት ዩኒቨርሲቲው ይህንን ሥልጠና ከወረዳው ለተወጣጡ ግንባር ቀደም ሴት አርሶ አደሮች መስጠቱ የህብረተሰቡን  ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡
ሥልጠናውን ከሠጡት ባለሙያዎች መካከል የግብርና ሣይንስ ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ይስሃቅ ከቸሮ  እንደገለፁት ይህ የተሻሻለ የወተት መናጫ ዘዴ በሀገራችን ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ሲተገበር የነበረ ነባር ቴክኖሎጂ ሲሆን በብዙ አካባቢዎች ተሞክሮ ውጤታማ  የሆነና  በተለያየ የአየር ንብረት ባላቸው ቦታዎች ተስማሚ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ቴክኖሎጂውን በአካባቢው ከሚገኙ ቁሳቁሶች  በቀላሉ ማዘጋጀት ስለሚቻልና ቴክኖሎጂው ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት ቆጣቢ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች በሰጡት  አስተያየት ከዚህ በፊት ወተት ለመናጥ ሲጠቀሙበት የነበረው ባህላዊ አሰራር   ከግማሽ እስከ ሙሉ ቀን እንደሚፈጅና ይህም ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን እንዲባክን የሚያደርግ እንደነበር ገልፀው ከሥልጠናው ባገኙት  በጽንሰ ሀሳብና በተግባር የተደገፈ ትምህርት መሠረት አዲሱ የወተት መናጫ ሥራቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማከናወን እንደሚያስችላቸውና ከአላስፈላጊ የጉልበትና የጊዜ ወጭ እንደሚታደጋቸው መረዳታቸውን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም ሠልጣኞቹ ዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ሽግግሩን ሥልጠና አመቻችቶ በመስጠቱ የተሰማቸውን ደስታ እና ምስጋና  ገልፀው ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ለሌሎች ሴት አርሶ አደሮች ያገኙትን ተሞክሮ እንደሚያካፍሉ ቃል ገብተዋል፡፡

ከሥልጠናው ጎን ለጎን የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ ከወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ ከእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ጽ/ቤት ኃላፊዎች እንዲሁም ከእንስሳትና ዓሳ ሀብት ጽ/ቤት ተጠሪዎች ጋር ውይይት ያካሄዱ ሲሆን በመጨረሻም ለእያንዳንዱ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤትና ለሠልጣኝ ሴት ሞዴል አርሶ አደሮች 40 የተሻሻሉ የመናጫ ቁሳቁሶች ተበርክተዋል ሲል የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዘግቧል፡፡

ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት