የቤተ-መፃህፍትና መረጃ ዳይሬክቶሬት በ2011 ዓ.ም ለተማሪዎችና ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ምቹ፣ ቀልጣፋና ዘመናዊ የቤተ-መፃህፍት አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡

በ2011 የትምህርት ዘመን በሁሉም ካምፓሶች  የተሻለ የቤተ-መፃህፍት አገልግሎት ለመስጠት በየካምፓሱ የሚገኙ ቤተ-መፃህፍትን ለንባብ ዝግጁ የማድረግ፣ መፃህፍትን በየፈርጁ የመለየትና የማደራጀት፣ አዳዲስ መፃህፍትን  አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ እንዲሁም ለቤተ-መፃህፍቱ ሠራተኞች ለተገልጋዮች ቀልጣፋና ዘመናዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና የመስጠት ተግባራት መከናወናቸውን የቤተ-መፃህፍትና መረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዓለምሰገድ ካሣሁን ተናግረዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ

በተጨማሪም በያዝነው ዓመት የተማሪዎችን የንባብ ባህል፣ ልምድና ፍላጎት ለማሳደግ እንዲሁም ከተለያዩ ደራሲዎችና አሳታሚ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት  በመፍጠር የንባብ ቀን በማዘጋጀት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ እንደሚሰራም ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡

 

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ለተማሪዎችና ለሌሎች የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የቤተ-መፃህፍት አገልግሎትን ምቹ እና  ዘመናዊ በማድረግ የንባብ ልምዳቸውን ለማዳበርና የንባብ ፍላጎታቸውን ለማነሳሳት ዝግጅት ተጠናቋል፡፡  ተገልጋዮች በጊዜ፣ በቦታና በቁሳቁስ እጥረት ሳይገደቡ በተለያዩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ  መሣሪያዎች በመታገዝ መፃህፍትንና ሌሎች መረጃዎችን በቀላሉ እንዲያገኙ ከህትመት  መፃህፍት በተጨማሪ የዲጂታል ቤተ-መፃህፍት በማዘጋጀት በቀጥታ አገልግሎቱን ከድህረ-ገፅ እንዲያገኙ ለማስቻል እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው በየካምፓሱ የሚከናወኑ የተለያዩ የግንባታ ሥራዎች የሚፈጥሩት አላስፈላጊ ድምፆች  የቤተ-መፃህፍት አገልግሎትን በከፍተኛ ሁኔታ እየረበሹ በመሆኑ በተለይም በዋናው ግቢ ቤተ-መፃህፍት አካባቢ የሚገኘው ጄኔሬተር ቤተ-መፃህፍቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጥ አስቸጋሪ ሆኔታ መፍጠሩን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በአንዳንድ ካምፓሶች በሚገኙ ቤተ-መፃህፍት  የመቀመጫ፣ የጠረጴዛና የመደርደሪያ እጥረት መኖሩን የጠቀሱት አቶ ዓለምሰገድ ችግሩን ለመቅረፍ ዩኒቨርሲቲው 50 ሚሊየን ብር መድቦ በግዢ ሂደት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ሰዓት 8 አገልግሎት በመስጠት ላይ እና 2 በእድሳት ላይ የሚገኙ በድምሩ 10 ቤተ-መፃህፍት ያሉት ሲሆን ከሶስት መቶ ሺህ በላይ የታተሙ፣  ከ15 ሺ በላይ ዲጂታል መፃህፍት  እንዲሁም ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ የምርምር ሥራዎች እንደሚገኙ ማወቅ ተችሏል፡፡