ቃልኪዳን አባይነህ የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንት

የተማሪዎች ኅብረት በ2011 የትምህርት ዘመን ከዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ፣ ከኮሌጅና ዳይሬክተር ጽ/ቤቶች፣ ከትምህርት ክፍሎችና ከመምህራን እንዲሁም ከተለያዩ አደረጃጀቶች ጋር በመሆን፣ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅና ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር አካባቢ ለመፍጠር መዘጋጀቱን ገለፀ፡፡

 

በአዲሱ የትምህርት ዘመን ወደ ዩኒቨርሲቲያችን የተመደቡ አዲስ ገቢና ነባር ተማሪዎችን  ለመቀበል የተማሪዎች መኝታ ክፍሎች እንዲሁም ሌሎች አገልግሎት መስጫ ማዕከላት  ጥገናና ጽዳት መከናወኑን ህብረቱ ማረጋገጡን የተናገረችው የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝደንት ተማሪ ቃልኪዳን  አባይነህ ተማሪዎች  በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ባሉ የተለያዩ ክበባት፣ ፎረሞችና አደረጃጀቶች በንቃት እንዲሳተፉ የተማሪዎች ህብረት ሥራ አስፈፃሚዎችና ተወካዮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በትጋት እንደሚሰሩ ገልፃለች፡፡ እንደ ፕሬዝደንቷ ገለፃ ኅብረቱ በዚህ ዓመት በዋናነት ሰላማዊ የትምህርት አካባቢ ከመፍጠር አኳያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመስራት ዝግጁ ነው፡፡

እንደ ፕሬዝደንቷ ገለፃ ተማሪው የሀገሩን ባህልና ታሪክ በመጠበቅ ከጥገኝነት፣ ከዘረኝነት፣ ከደባል ሱሰኝነትና ከኋላቀር  አስተሳሰብ የፀዳ፣ በራሱ የሚተማመን፣ ሀገር ወዳድና በመልካም ሥነ-ምግባር የታነፀ እንዲሆን በተማሪዎች ዲስፕሊን ዙሪያ በርካታ ሥራዎች ይሰራሉ፡፡ የፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥም  ከዩኒቨርሲቲዉ የሥርዓተ ፆታ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር የሴቶችን ክበብ በአዲስ መልክ በማዋቀር እንዲሁም ዜሮ ፕላንን ሙሉ በሙሉ ሴት ተማሪዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ እንዲሁም በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ እንዲሳተፉ የአቅም ግንባታ ስራዎች ይከናወናሉ ብላለች፡፡

በምግብ አገልግሎት ኮሚቴነት የሚያገለግሉ ተማሪዎችን በጥንቃቄ መምረጥና ከምግብ አገልግሎት ኃላፊዎች፣ አስተባባሪዎች፣ ከካፍቴሪያ እና ከምግብ ቤት ሠራተኞች ጋር ተባብረዉ በአግባቡ መስራት እንዲችሉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ፤ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች  ተገቢውን  አገልግሎት መስጠታቸውን መከታተልና ለአዲስ ገቢ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ከልዩ ፍላጐት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ጋር በመሆን የዶርምና የመማሪያ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ህብረቱ በዚህ ዓመት ከሚሠራቸው ዕቅዶች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሆኑ ፕሬዝደንቷ ገልፃለች፡፡

የተማሪዎች ኅብረት ፕሬዝደንቷን ጨምሮ ፣ 6 ም/ፕሬዝደንቶችና 21 ሥራ አስፈፃሚዎች ያሉት ሲሆን በየካምፓሱ አንድ ም/ፕሬዝደንትና እንደካምፓሱ ስፋት ሌሎች ሥራ አስፈፃሚዎች ተመድበው በየሳምንቱ ውይይት እንደሚያካሂዱ ማወቅ ተችሏል፡፡