የይዞታ ልማትና መገልገያ መሳሪያዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት በ2011 በጀት ዓመት በዩኒቨርሲቲው ግቢ የሚያካሂዳቸውን የተለያዩ የልማት ሥራዎች ለማሳካት ተግቶ እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡

የይዞታ ልማትና መገልገያ መሳሪያዎች አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መተኪያ አዛዥ እንደገለፁት በባለፈው በጀት ዓመት ዳይሬክቶሬቱ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን ተናግረው በዋናነት ሦስት የንጹህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮና ውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች አጥር ሥራ፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ኮብል ንጣፍ ሥራ፣ የጽዳት ሠራተኞች ማረፊያ ቤት ግንባታ፣ 100 የሚጠጉ የመብራት ፖሎች ግዢና የዝርጋታ ሥራ፣ ለኢትዮ- ፊሸሪ የመምህራን መኖሪያ ቤቶች ጀኔሬተር ግዢና መስመር ዝርጋታ ሥራዎች ዋና ዋነዎቹ ናቸው፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲው በተደጋጋሚ የውሃ መቋረጥ ችግር ይታይ እንደነበር አስታውሰው በ2010 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ለችግሩ መፍትሄ ሲባል የንፁህ መጠጥ ውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቆ ለአገልግሎት በመብቃቱ ችግሩ በከፊል መቅረፍ ተችሏል፡፡ ዳይሬክቶሬቱ በተያዘው በጀት ዓመትም ተጨማሪ 4 የውሃ ጉድጓድ ቁፋሮ እንደሚከናውን የገለፁት ዳይሬክተሩ ከ 1 ሚሊዬን ብር በላይ በጀት ተመድቦ ከዞኑ መዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ጋር በመሆን እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የዩኒቨርሲቲውን የሥራ አካባቢ ለመማር ማስተማሩም ሆነ ለሌሎች ተግባራት ምቹና ማራኪ የማድረግና የተለያዩ የግንባታና የጥገና ሥራዎች በትኩረት እየተሰሩ ሲሆን ሥራዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ዳይሬክቶሬቱ በቁርጠኝነት ይሰራል ብለዋል፡፡

ዳይሬክቶሬቱ ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ከሚያከናውናቸው በርካታ የልማት ተግባራት መካከል ያረጁ ህንፃዎች እድሳት፣ የዙሪያ አጥር እድሳትና ሥራ፣ የመምህራን ማረፊያ ቤት እድሳት፣ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ኮብል ንጣፍ፣ የተማሪዎችና የመምህራን መጸዳጃ ቤት ግንባታና ጥገና፣ የውሃና የመብራት ስርጭትን ማዳረስ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡