ዩኒቨርሲቲው በግብርና ሳይንስ ዘርፍ በግብርና ሳይንስ ኮሌጅ ምርምር ዩኒቲ እና በዘርፉ ምርምር ማዕከላት በ2010 በጀት ዓመት ካከናወናቸው የምርምር ሥራዎች መካካል የቡና ዝርያዎችን ማሻሻል፣ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የመስኖ አጠቃቀምን ማጎልበት፣ የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ፣ በሐይቆች አካባቢ የሚከሰት የአፈር ጨዋማነትን መከላከል፣ የሙዝ ግብይትን ማጎልበት፣ የንብ እርባታ ዘዴዎችን ማዘመን እንዲሁም የሰብል ልማትና የእንስሳትና ዓሳ ሀብትን ማሻሻል የሚሉ ይገኙበታል፡፡

የኮሌጁ ምርምር ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ደረጀ ፀጋዬ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው ከቡና ምርት ምርታማነት ጋር በተያያዘ ከጂማ ዩኒቨርሲቲ ግብርናና ምርምር ማዕከል ጋር በመሆን በጋሞ ጎፋ ዞን በሚገኙ ቡና አብቃይ በሆኑ አካባቢዎች ቡና በሰፊው እንዲመረት የሚያስችል የቡና ዝርያዎችን አሻሽሎ ለአርሶ አደሮች የማስረከብ ሰፊ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዚህም በደንቢሌ ቀበሌ፣ በቦረዳ፣ በምዕራብ አባያ እና በደምባ ጎፋ ወረዳዎች የተሸሻሉ የቡና ዝርያዎች እንዲሰራጩ ተደርጓል፡፡

እንደ ጽ/ቤቱ ኃላፊ ማብራሪያ ሀገር በቀል የሰብል ዝርያዎችን ከማጎልበትና ከማስፋት አንፃር በርካታ ምርምሮች እየተካሄዱ ሲሆን በዚህ ረገድም በኮሌጁ ሽፈራው ተብሎ በተቋቋመ ፕሮጀክት ጥናቶች እየተካሄዱ ይገኛል፡፡ ከእንስሳት ምርምር ጋር በተገናኘም ከተለያዩ አካባቢዎች የበግና የወተት ላሞች ዝርያዎችን በማምጣት ሰው-ሰራሽ በሆነ ዘዴ የማዳቀልና ማላመድ ሥራዎች ተሰርተው ለሙከራ በቦንኬ ወረዳ ለሚገኙ የተወሰኑ አርሶ አደሮች አዲሶቹን ዝርያዎች ማከፋፈል መቻሉን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

ከዓሳ ሀብት ጋር ተያይዞ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ምርምር ማዕከል የዓሳ ምርትን ለማሻሻልና ለማስፋት ከባለፈው ዓመት የካቲት ወር ጀምሮ ሰው-ሰራሽ የውሃ ገንዳዎችን እያዘጋጀ የሚገኝ ሲሆን ይህም ከብዝሃ- ህይወት ተመራማሪዎች ጋር በጋራ የሚሰራ መሆኑን ዶ/ር ደረጃ ጠቅሰዋል፡፡ በቀጣይም የተለያየ የአየር ንብረት ባሉባቸው ቦታዎች ሊኖሩ እንዲሁም
ሰው-ሰራሽ በሆኑ ዘዴዎች ሊራቡ የሚችሉ የዓሳ ዝርያዎችን መለየት ላይ ትኩረት ያደረጉ ጥናቶች ይሠራሉ ብለዋል፡፡

በኮሌጅና ምርምር ማዕከላት ደረጃ ለምርምር ሥራ የሚበጀት በጀት ማነስና በወቅቱ አለመድረስ፣ የግዥዎች በወቅቱ አለመፈፀም፣ ለምርምር ሥራ ተብለው የተገነቡ ቤተ-ሙከዎች ለሥራው ምቹ አለመሆንና በአግባቡ አለመደራጀታቸው፣ መምህራን የምርምር ሥራዎችን ጀምረው ያለመጨረስና ለትምህርት ሲሄዱ የጀመሩትን የምርምር ሥራ መቋረጥና ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ እንዲሁም የተሸከርካሪ እጥረት በምርምሩ መስክ የላቀ ውጤት እንዳይመዘገብ ያደረጉ ማነቆዎች መሆናቸውን ዶ/ር ደረጀ ገልፀዋል፡፡

በ2010 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የዩኒቨርሲቲዎች የግብርና ሳይንስ የምርምር ዘርፍ የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ከ44 ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በስራ አፈጻጸማቸው የተሻሉ ከሆኑ 4 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መካተት መቻሉን የገለፁት ኃላፊው በያዝነው በጀት ዓመትም በተለይ በእንስሳት፣ በወተትና ሥጋ ከብት እርባታ፣ ቄራ አካባቢ በሚደረግ የስጋ አቅርቦት፣ የሽፈራውን ቅጠል በመመገብ የዶሮ ጫጩቶችን የማራባት ዘዴ፣ ከሰው ወደ እንስሳና ከእንስሳ ወደ ሰው የሚተላለፉ በሽታዎችን መከላከል፣ በንብ እርባታ፣ በሰብል ልማትና በጋማ ከብቶች ላይ ያተኮሩ ምርምሮች በስፋት እንደሚካሄዱ አስተባባሪው ጠቁመዋል፡፡

በኮሌጁ ባለፉት 2 ዓመታት እየተካሄዱ ከነበሩ 42 ምርምሮች አራቱ የተጠናቀቁ ሲሆን ሁለቱ የምርምር ሥራዎች ደግሞ በምርምር ጆርናሎች ላይ መታተም ችለዋል፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም 15 የሚሆኑ ምርምሮች ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡