የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቅና በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን አገር በሚገኝ ‘‘COMSOL MULTIPHYSICS’’ በተባለ ድርጅት የአፕሊኬሽን መሐንዲስ የሆኑት ዶ/ር ተመስገን ማርቆስ ከቴክኖሎጂ እና ከውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ከተወጣጡ ተማሪዎች ጋር ከትምህርት የሚገኝ እውቀት ከተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ኩነቶች ጋር ትሥሥራዊ እይታ ሲፈጥርዎች ትስስር ለውጤታማ ሥራ እና ለስኬታማ ህይወት ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ኅዳር 10/2011 ዓ/ም ገለፃዊ ተሞክሮ የማጋራት ውይይት አካሂደዋል፡፡ ምስሉን ለመመልከት ከዚህ ይጫኑ::

ፕሮግራሙ ተማሪዎች ከአካዳሚክ እውቀት ባሻገር በሌሎችም ተግባራት በተለይም በሂሳብና በአፕላይድ መካኒክስ ላይ በንቃት ተሳትፎ በማድረግ ህይወታቸውን እንዴት ስኬታማ ማድረግ እንደሚችሉ ግንዛቤ ለመፍጠርና ልምድና እውቀታቸውን ለማካፈል የተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ተመስገን ገልፀዋል፡፡ የሂሳብ ስሌቶች አተገባበር እና የምህንድስና ስትራክቸር መመሪያዎች ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በመፍታት ለሰዎች ምቹ ማድረግ የሚያስችል አቅም ይፈጥራልም ብለዋል፡፡

ዶ/ር ተመስገን በቀድሞው አርባ ምንጭ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በ1994 ዓ/ም የመጀመሪያው የሲቪል ምህንድስና ምሩቅ እና የወቅቱ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካን አገር በሚገኝ ‘‘Simulation Software’’ አበልፃጊ በሆነው COMSOL MULTIPHYSICS ድርጅት እየሠሩ ይገኛል፡፡ ሊተገበሩ የሚችሉ የሂሳብ አፕሊኬሽኖች በመጠቀም በምህንድስና ዘርፍ ያሉ ችግሮችን ማቃለል በሚያስችሉ ሀሳቦች ዙሪያ በድርጅቱ ያለውን እውቀትና ተሞክሮ ለማጋራት በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሣይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር አለማየሁ ጩፋሞ ይህን መሰል ልምድ ማካፈል እና የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ተማሪዎች በግቢ ውስጥ ባላቸው ጊዜና በሥራው ዓለም ሊገጥማቸው በሚችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ግንዛቤ ለመፍጠር ድርሻው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ተመስገን በግላቸው ያደረጉትን አርአያነት ያለው ተግባር በማጠናከርና ሌሎችንም በማስተባበር በቀጣይም በተለያዩ ዘርፎች መሰል ድጋፎችን አጠናክረው ለተቋሙ ተልዕኮ እውን መሆን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አበክረው አሳስበዋል፡፡

የተለያዩ ሥራዎች ነጥለን መሥራት ስንፈልግ የሚያጋጥሙ የተለያዩ ተግዳሮቶች እንዳሉ ይታመናል፡፡ Multiphysics ደግሞ በተለያየ የሣይንስ ዘርፍ ያለውን ዕውቀት የሚያቀናጅ በመሆኑ ሂደቱን ለማቃለል ያስችላል፡፡

ሂደቱን ለማቃለል ያስችላል፡፡ በተጨማሪ ውጤታማና ወጪ ቆጣቢ በሆነ ሁኔታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች መፍታት የሚያስችሉ ስልቶችን ከአካዳሚክ እውቀት ጋር በማቀናጀት ለመተግበር Multiphysics ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

በማብራሪያው Soft skills በማኅበራዊ ዘርፍ፣ አብሮ የመሥራት አቅም፣ ተገቢ ተግባቦት መፍጠር፣ የአመራርነት አቅም፣ ሥራን የማከፋፈል አቅም እና ሌሎች መሥራት መቻላቸውን በማወቅና መሰል ሂደቶችን በመገንዘብ ራስን የማስተማር ችሎታ እንዲሁም የተወዳዳሪነት መንፈስ በማጎልበትና ግንኙነቶችን በማዳበር ለስኬት መብቃት ላይ ገለፃና ውይይት ተደርጓል፡፡

በተፈጥሮ ኡደቶች ላይ የማይለያዩ ሥርዓቶችን ማቀናጀት የሚያስችል ተግባር ተኮር የምህንድስና ስልቶች ላይ ጥሩ ግንዛቤ የሚፈጥር ከመሆኑም ባለፈ ቀደም ሲል በራሳቸው ትምህርት ብቻ ተወስነው ውጤታማ ለመሆን የሚደረገውን ሁኔታ በመቀየር በሌሎች የትምህርት ዓይነቶችም በፍላጎት እውቀት እንዲቀስሙ የሚያግዝ ነው፡፡ ከዚህ ምሁር ለወደፊቱ ልምድ መቅስምና ጥሩ ራዕይ መሰነቅ መቻላቸውን ገልፀው በሂደቱ ከሚገኘው ተጨማሪ እውቀት ባሻገር ከሌሎች ተማሪዎች ጋር መልካም ግንኙነት ለመፍጠር እድል የሚከፍት በመሆኑ በተሞክሮ ልውውጡ ደስ እንደተሰኙ ተሳታፊ ተማሪዎች ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ተመስገን በቀጣይም የዩኒቨርሲቲውን ተልዕኮ በሚፈለገው ጥራትና አግባብነት በማስተግበር ለአገራዊ እድገቱ አስተዋጽኦ እንዲኖረው በሚደረገው ሁለንተናዊ ጥረት የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በቴክኖሎጂ እና ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩቶች ከሚገኙ የተለያዩ የትምህርት ክፍሎች የተወጣጡ ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡