ዓለም አቀፍ የነጭ ሪባን ቀን ተከበረ

‹‹በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስወገድ የወንዶች አጋርነትን ማጠናከር›› በሚል መሪ ቃል ዓለም ዓቀፉ የነጭ ሪባን ቀን በዩኒቨርሲቲው ኅዳር 21/2011 ዓ/ም ተከብሯል፡፡ በዓሉ ሲከበር በዓለም ለ28ኛ በአገራችን ደግሞ ለ13ኛ ጊዜ ነው፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

የዩኒቨርሲቲው የሥርዓተ-ፆታ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሪት ሰናይት ሣህሌ በዓሉን አስመልክቶ ሲናገሩ የነጭ ሪባን ቀን በተለያዩ ዝርዝር ዓላማዎች ቢከበርም በዋናነት ‹በሴቶች ላይ የሚደርሱ ፆታዊ ጥቃቶችን እንቃወማለን› የሚል መልዕክት ያለው ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ከኅዳር 16 - 30 ወንዶች ነጭ ሪባን ደረታቸው ላይ በማድረግ በግል በሴቶች ላይ ጥቃት ላለመፈፀም፣ ሲፈፀም አይቶ ዝም ላለማለት እና ኃላፊነት በመውሰድ ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስቆም መወሰናቸውን የሚያረጋግጡበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ወ/ሪት ሰናይት በአገራችን የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉ ከፍተኛ አመራሮችና አስፈፃሚ አካላት እኩሌታው ሴቶች በሆኑበት ወቅት የዘንድሮው የነጭ ሪባን ቀን መከበሩ በዓሉን ልዩና ደማቅ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በነጭ ሪባን ቀን ፅንሰ ሀሣብና በዩኒቨርሲቲው ነባራዊ ሁኔታ ላይ አጭር ውይይት የተደረገ ሲሆን በየዓመቱ ቀኑን ከመዘከር በዘለለ በዩኒቨርሲቲው ተጨባጭ ለውጦችን የሚያመጣ አመራርና ማኅበረሰብ ሊፈጠር እንደሚገባ ተገልጿል፡፡
በተለይም ሴት ተማሪዎችን ከትንኮሳና ጥቃት በመከላከልና ተገቢውን የማበረታቻ ሥርዓት በመዘርጋት በአመርቂ ውጤት ማስመረቅ እንዲሁም ለሴት መምህራንና ሠራተኞች ሠላማዊ የሥራ አካባቢን በመፍጠር ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል በአስተያየቶቹ አፅንኦት ተሰጥቶታል፡፡
የነጭ ሪባን ቀንን ከማክበር ጎን ለጎን በፕሮግራሙ በ2010 የትምህርት ዘመን 2ኛ አጋማሽ ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገቡ ሴት ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት የዕለቱ የክብር እንግዳ ከሆኑት የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም እጅ ተበርክቶላቸዋል፡፡ ተሸላሚ ተማሪዎቹ 13 ሲሆኑ ከ3.79 – 4.00 ነጥብ ያስመዘገቡ ናቸው፡፡
የክብር እንግዳዋ ዶ/ር ሂሩት ለተሸላሚ ተማሪዎች መልዕክት ሲያስተላልፉ ሁለት ነገሮች ሴትን ልጅ ወደ ኋላ ይጎትቷታል፤ እነዚህም ሴት በመሆኗ ምክንያት የሚያርፍባት ተደራራቢ የኃላፊነት ጫና እና የማኅበረሰቡና የራሷ የሴቷ አመለካከት ናቸው ብለዋል፡፡ ዶ/ር ሂሩት የራሳቸውን ህይወት ለተሞክሮ በመጥቀስ ሴቶች እነዚህን ውጫዊና ውስጣዊ ጫናዎች ማሸነፍና አቅማቸውን በተግባር ማሳየት እንደሚገባቸው ብሎም እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
ምንም እንኳ ሴቶች በማኅበረሰብ ምጣኔ ግማሹን ያህል ቢሆኑም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥም ሆነ በሥራ ዓለም በሚገጥማቸው ተስፋ አስቆራጭና ፈታኝ ሁኔታዎች መድረስ ከሚገባቸው ስኬት ይሰናከላሉ ያሉት ዶ/ር ሂሩት ነገር ግን መሰል ችግሮችን ተቋቁመው ከፍተኛ ቦታ የደረሱ ሴቶችን አርአያ በማድረግ ሴት ተማሪዎች ህልም ሊኖራቸውና ለህልማቸውም ያላቸውን አቅም በአግባቡ አሟጠው መጠቀም እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡