ዩኒቨርሲቲው በ2011 በጀት ዓመት የግዥ እና የፋይናንስ አሠራርን ለማሻሻል እንዲሁም ለተማሪዎች አስፈላጊ የሆኑ መሠረት ልማቶችን ለማሟላት በትኩረት እየሠራ መሆኑን የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ጽ/ቤት ገለፀ፡፡

የአስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ዶ/ር መልካሙ ማዳ እንደገለጹት በሩብ ዓመቱ ከታዩ ስኬቶች መካከል ረጅም ጊዜ የወሰደው የJEG ድልድል ውጤት ለሠራተኞች ይፋ መሆኑና የተማሪዎች ቀለብ ጨረታና ግዥ መካሄዱ የሚጠቀሱ ሲሆን በአንፃሩ በአገራዊ ለውጦች ምክንያት የተማሪዎችና የመምህራን ዝውውር ፍላጎት መጨመሩ ለመማር ማስተማሩ ተግዳሮት ፈጥሯል፡፡
እንደ ዶ/ር መልካሙ ገለፃ በግዥ መመሪያው ምክንያት በተለይም ለመማር ማስተማር የሚያስፈልጉ ግብዓቶች በሙሉ በማዕቀፍ ግዥ ውስጥ መሆናቸው በወቅቱ እንዳይደርሱና በጥራት እንዳይቀርቡ በማድረጉ የግዥ ሥርዓቱ ቀልጣፋ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡
ከሀብት ብክነት ጋር ተያይዞ ሠራተኛው ግዥ መፈፀሙን እንጂ የተገዛበትን ዓላማ ተከታትሎ የሚያስፈፅም አካል ባለመኖሩ የተገዙ ዕቃዎች በትክክል ለታለመላቸው ዓላማ አለመዋልና መልሶ የመጠቀም ችግር የሚስተዋል መሆኑን ዶ/ር መልካሙ ገልፀዋል፡፡ ፋይናንስ አካባቢ የሚያጋጥሙ የክፍያ መዘግየትና የቢሮክራሲ ችግሮችን ለመፍታት የወረቀት አሠራርን አስቀርቶ ወደ ኤሌክትሮኒክ ሲስተም ለመቀየር መታቀዱንም ተናግረዋል፡፡
አዲሱ የሥራ ምደባን በተመለከተ ለሁሉም ሠራተኞች ይፋ የተደረገ ሲሆን 20% የሚሆኑ ሠራተኞች ቅሬታ አቅርበው በዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት በተቋቋመው ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡ በኮሚቴው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ሠራተኛ ለሰው ሀብትና ፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴር ቅሬታውን ማቅረብ ይችላል፡፡ የቅሬታ ማስተናገድ ሥራው ሲጠናቀቅ ሠራተኞች የምደባ ደብዳቤ የሚደርሳቸውና ወደ ተመደቡበት ሥራ የሚገቡ መሆኑን ዶ/ር መልካሙ ተናግረዋል፡፡
እንደ ዶ/ር መልካሙ ማብራሪያ በየካምፓሶች የሚታየውን የውኃ እጥረት ለመቅረፍ የከተማው ውኃ ከከተማው ነዋሪ ተርፎ ሊዳረስ ስለማይችል በየካምፓሶች የጉድጓድ ውኃ ቁፋሮና ዝርጋታ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ ዋናው ግቢ፣ ሳውላና ኩልፎ ካምፓሶች ቁፋሮ ተጠናቆ በቅርቡ የውኃ መስመራቸው ከዋናው መስመር ጋር የሚገናኝ ሲሆን በጫሞ፣ አባያና ነጭ ሳር ካምፓሶች ጥናቱ ተጠናቆ ጨረታ ከወጣ በኋላ ወደ ቁፋሮ ይገባል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲው ውስጥና ከውጭ የሚከሰቱ የፀጥታ ችግሮችን ለመቅረፍ ተማሪዎችንና የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማሳተፍ እየተሠራ መሆኑን ዶ/ር መልካሙ ተናግረዋል፡፡