ዩኒቨርሲቲው ለ5ኛ ጊዜ ያሰለጠናቸውን 76 የህክምና ዶክተሮች ኅዳር 22/2011 ዓ/ም በደማቅ ሁኔታ አስመርቋል፡፡
የዩኒርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጡ የትምህርት ፕሮግራሞችና የሚካሄዱ ምርምሮች የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱና ይበልጥ ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆን ይገባቸዋል ብለዋል፡፡ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በአገር አቀፍ ደረጃ የተቀመጠውን የትምህርት ጥራት፣ አግባብነትና ተደራሽነት ግብ ለማሳካት በትኩረት እየሠራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

ዩኒቨርሲቲው የጤና ዘርፍ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል በመምህራን ልማት ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝደንቱ ኮሌጁ 127 መምህራን  እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን 69ኙ 2ኛ ዲግሪ፣ 11ዱ 3ኛ ዲግሪ እና 41ዱ የስፔሻሊቲ መ/ራን  ደረጃቸውን ሊያሻሽል ትምህርት በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ ፕሬዝደንቱ ማብራሪያ ዩኒቨርሲቲው ከአርባ ምንጭ ሆስፒታልና አጎራባች የጤና ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር፣ በማኅበረሰቡ ጤና መሻሻል ላይ ትኩረት ያደረጉ ምርምሮችን በማከናወንና የማኅበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በመሥራት ላይ ነው፡፡
ፕሬዝደንቱ በህክምና ትምህርት የሴት ተማሪዎችን ተሳትፎ በተመለከተ በ2009 ዓ/ም ከነበሩት 58 የህክምና ዶክትሬት ምሩቃን የሴት ምሩቃን ቁጥር 1 ብቻ የነበረ ሲሆን በ2011 ዓ/ም ከተመረቁት 76 የህክምና ዶክተሮች የሴት ምሩቃን ቁጥር 18 መድረሱ  የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ምሩቃን በዩኒቨርሲቲው ያገኙትን ዕውቀትና ክህሎት ከሥራው ዓለም ጋር አዋህደው የማኅበረሰቡን ጤና ለማሻሻል የበኩላቸውን አስተዋፅኦ በማበርከት ለአገራችን ህዳሴ ታላቅ ሚና እንዲጫወቱም አሳስበዋል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ በድሩ ሂሪጎ በበኩላቸው እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው  ከመማር ማስተማር ባሻገር የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ለመቀነስ፣ የወባ በሽታን ለመከላከል እንዲሁም መሰል የጤና መሻሻል ሊያመጡ የሚችሉ አገር አቀፍ ምርምሮችን ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ሲሆን እየተገነባ ያለው የዩኒቨርሲቲው ዘመናዊ የማስተማሪያና ሪፈራል ሆስፒታል ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር ጥራት ያለው የጤና ትምህርትና የህክምና አገልግሎት ለማህበረሰቡ ለመስጠት ያስችላል፡፡
ዓለም የሚፈልገውን ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ከማፍራት አንፃር በአገራችን ትምህርትና ሥልጠና አቅርቦት፣ ተገቢነትና ጥራት ላይ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች አሉ ያሉት የኢፌዴሪ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር እና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ሂሩት ወ/ማርያም ያለነው በታዳጊና ኢኮኖሚዋ ባልዳበረ አገር እንደመሆኑ መጠን ምሩቃን ችግሮችን በሰከነ መንፈስ በመጋፈጥ በድል መወጣት፣ ቀና አስቢነትንና ትህትናን መላበስ እንዲሁም በአሸናፊነት እና በእችላለሁ ስሜት ተነሳሽነት የወገናችውን ህይወት የሚቀይር ሃሳብና አሠራር ሊቀይሱ ይገባል፡፡
‹‹ዛሬ ተንብዩ፤ ለነጋችሁ ያለእረፍት ሥሩ፡፡ የምትይዙት ጓደኛ የምታዩት ፊልም ሁሉ ከህልማችሁ እና መድረሻችሁ ጋር የተገናኘና ግባችሁ ላይ ለመድረስ የሚያግዛችሁ መሆኑን አረጋግጡ›› ያሉት ሚኒስትሯ ዘረኝነት፣ ሌብነት እና ራስ ወዳድነት ከአገራችን ወግና ባህል የወጡ በመሆኑ ልትታገሏቸው ይገባል ብለዋል ፡፡
የኢትዮጵያ የህክምና ማህበር ተወካይ እንዲሁም የእለቱ ተጋባዥ እንግዳ ዶ/ር መስከረም አለቃ በበኩላቸው የተመረቃችሁበት ሙያ ትልቁን የሰው ልጅ የማዳን ተግባር በመሆኑ በሥራው ዓለም የሚጠብቋችሁን ተግዳሮቶች በትጋት በመወጣት ለወገናችሁን ጤና መሻሻል ልትሰሩ ይገባል በማለት  ለአገሪቱ ጤና መሻሻል በጋራ ለመሥራት ለምሩቃኑ በማህበሩ ሥም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የሜዳሊያ ተሸላሚ መሆኑ እንዳስደሰተው የገለፀውና 3.54 በማምጣት የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ የሆነው ምሩቅ
ዶ/ር መሠረት ሙሉ በቀጣይ የማህፀንና ፅንስ ሐኪም መሆን እንደሚፈልግና የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ ሃላፊነት እንደሚጠብቀው ተናግሯል፡፡
3.46 የማዕረግ ውጤት በማምጣት ሴቶች በህክምና ትምህርት ዘርፍ የተሻለ ተሳትፎ መኖሩን ጥሩ ማሳያ የሆነችው ተመራቂ ዶ/ር ትዕግስት ገረሱ የእናቶችንና ህፃናትን ሞት ሊቀንሱ የሚችሉ በቂ ምርምሮችን በማከናወን ባለት ዕውቀትና ክህሎት ማህበረሰቡን ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነች ገልፃለች፡፡