ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግሩን ወደ መካከለኛ ደረጃ ለማምጣት ትኩረት ሰጥታ እየሠራች እንደምትገኝ ተገለጸ

በቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ አዘጋጅነት አገራችን ኢትዮጵያ እየተገበረች ያለችውን የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር (Structural Transformation) እንዳይጠናከር ያደረጉ ማነቆዎች፣ የአገሪቱ የእድገት ደረጃ፣ የመዋቅራዊ ሽግግሩ ቀጣይ ዕቅድ እንዲሁም በገበያ ጥናት ላይ የሚስተዋሉ ለውጦችና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ የጥናት ውጤት ቀርቦ ከዘርፉ ባለሙያዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ኅዳር 13/2011 ዓ.ም ውይይት ተደርጓል፡፡ የጥናቱ አቅራቢና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ማኅበር አባልዶ/ር ሰኢድ ኑሩ እንደገለጹት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከማስተማር ጎን ለጎን የሀሳብ ማፍለቂያ መድረክ በመሆን የዳበሩ ሀሳቦችን ወደ ህብረተሰቡ እንዲያደርሱና የዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የዳበሩ የውይይት ሀሳቦችን በማንሸራሸር ለአገሪቱ የሚበጀውን የኢኮኖሚ ምህዳር ለማምጣት በቅንጅትና በትጋት ሊሠሩ ይገባል፡፡ መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማሳካት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ያስቀመጣቸው ግቦች ቢኖሩም ተቋማዊና ሥርዓታዊ ለውጥ ማምጣት ወሳኝ ሚና እንዳለው ዶ/ር ሰኢድ አብራርተዋል፡፡
ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት ቀጣይነት፣ ከፍተኛ የሀብት ክምችትን ምርታማ ማድረግ እንዲሁም በዘላቂነት ከድህነት ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር የመጀመሪያው ሂደት የሚሉ ነጥቦች በጥናቱ ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ እነዚህን ወደ ተጨባጭ መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው የሀሳብ ልውውጥ ከግብ እንዲደርስ የዳበሩ የውይይት ሀሳቦችን በማፍለቅ በአንድ ወጥ መመሪያና የዲሲፕሊን ሥርዓት ብቻ ከማስኬድ ይልቅ የጋራ ውይይት በማድረግ ወደ መፍትሄው መምጣት እንደሚቻል ተገልጿል፡፡
የኢኮኖሚ ምህዳሩ ወደ መካከለኛ ደረጃ መዝለቅ እንዲችልና መዋቅራዊ ሽግግሩ ወደ ታለመለት የአመራረት ሂደት እንዲቀየር ትክክለኛ የገቢ ሥርዓት መፈጠርና ዝቅተኛ ምርታማነት ወደ ከፍተኛ ምርታማነት መሸጋገር እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ደረጃ ፈጣን ዕድገትን እያስመዘገበች ትገኛለች፤ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም መዋቅራዊ ሽግግሩን ለማስቀጠል ትኩረት በመስጠትና የኢኮኖሚ ሥርዓቱን በመቀየር አገሪቱን ወደ መካከለኛ የእድገት ደረጃ ለማድረስ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
በውይይቱ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንትን ጨምሮ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው የጋሞ ጎፋ ዞን የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡