የግዥና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ከሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር ከሁሉም ካምፓሶች ለተወጣጡ የግዥና ንብረት አስ/ዳይሬክቶሬት ሠራተኞች በሙስና ፅንሰ ሀሳብ፣ በሙስና ወንጀል ህጎች፣ በግዥ ባለሙያዎች ሥነ-ምግባር፣ በግዥ ሂደት እንዲሁም በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ኅዳር 18/2011 ዓ.ም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና  ሰጥቷል፡፡

የስልጠናው ዓላማ በዩኒቨርሲቲው በግዥ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎችን ሙያዊ ብቃት በማዳበር የግዥ አፈፃፀሙ ቀላል፣ ፈጣን እንዲሁም በታቀደው መሠረት የግዥ ፍላጎትን የሚያሟላ እንዲሆን ማስቻል ነው፡፡
የሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ላቴኖ ላንጋና ባቀረቡት የስልጠና ሰነድ እንደተብራራው ሙስና በመንግሥትና በህዝብ ሀብትና ንብረት ላይ ስርቆት መፈጸም፣ ዝርፊያ ማካሄድ፣ ማጭበርበር፣ ሕግና ሥርዓትን ተከትሎ ከመሥራት ይልቅ በዝምድና፣ በትውውቅ፣ በጐሳ፣  በፖለቲካ ወይም በኃይማኖት ወገንተኝነት ላይ ተመርኩዞ አድልኦ መፈፀም፣ ፍትህን ማጓደልና ሥልጣንና ኃላፊነትን በህገ-ወጥ መንገድ የጥቅም ማግኛ የማድረግ እኩይ ተግባር ነው፡፡
የሙስና ወንጀል በተለያዩ ዘርፎች የሚከሰት፣ በብዙ መልኩ የሚገለጽ እና በተለያዩ ደረጃዎች በሚገኙ ሰዎች የሚፈፀም መሆኑን የተናገሩት አሰልጣኙ ሙስና ከሌሎች ወንጀሎች ጋር ሲነጻጸር የአፈፃፀሙ ሂደትና ስልት ውስብስብ መሆን፣ በአብዛኛው ለጉዳዩ ባለቤት ነኝ ባይ አለመኖር፣ የፈፃሚዎቹ ማንነት፣ በብዙ ሰዎች ዘንድ እንደ ነውር አለመታየቱና ሙስናን በመዋጋት ተግባር ላይ የተሠማሩትን ማሸማቀቁ ወንጀሉን ለመዋጋት ከባድ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
በንብረት አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ሰነድ ያቀረቡት የንብረት አስተዳደር ቡድን መሪ አቶ ዘላለም ጌታቸው እንደተናገሩት  የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች በእጃቸው ያለውን የመንግሥት ንብረት በጥንቃቄ መያዝ፣ መጠቀም፣ መቆጣጠርና የንብረቱ የአገልግሎት ጊዜ ሲያበቃ በወቅቱና በተገቢው መንገድ ማስወገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የንብረት ብክነት ለማስወገድና ቋሚ አላቂንብረቶች ቁጥጥር የተሟላ ለማድረግ መዛግብቶቹ  የውስጥ ቁጥጥር ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል፡፡
ከተሳታፊዎች በቀረቡ አስተያየቶችና ጥያቄዎች መሠረት የጋራ ውይይት የተካሄደ ሲሆን ከአሰልጣኞች ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶበታል፡፡ ሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት ስልጠናው አስተማሪና ግንዛቤ የሚያስጨብጥ እንዲሁም በተግባር ለሚያከናውኑት ሥራ አጋዥ እንደሚሆን ገልፀዋል፡፡
ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት