በዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች አገ/ማ/ዳይሬክቶሬት አስተባባሪነት 26ኛው የአካል ጉዳተኞች ቀን ‹‹አካል ጉዳተኞችን በማብቃት አካታችነትን እና እኩልነትን እናረጋግጥ›› በሚል መሪ ቃል ኅዳር 24/2011 ዓ/ም በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሯል፡፡
በዓሉ ሲከበር በዓለም ለ27ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ26ኛ ጊዜ ሲሆን በአገር አቀፍ ደረጃ በደቡብ ክልል ርዕሰ መዲና ሀዋሳ ከተማ ተከብሯል፡፡ ምስሎቹን ለማየት እዚህ ይጫኑ::

በዩኒቨርሲቲው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች የትምህርት ተሳትፎና ውጤታማነት ከዓመት ወደ ዓመት መሻሻል ማሳየቱን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝደንት ዶ/ር ዳምጠው ዳርዛ ገልፀዋል፡፡ በአገልግሎት መስጫ፣ በመማሪያና ማደሪያ ህንፃዎች፣ በአቅም ግንባታና የአመራርነት ሚናቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች መኖራቸውን የተናገሩት ፕሬዝደንቱ በቀጣይም በድጋፍ፣ ልምዶችን በመቀመርና ምቹ አካባቢን በመፍጠር ውጤታማ እንዲሆኑ የማድረጉ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡ መንግሥት የአካል ጉዳተኞችን አቅም ለማሳደግ፣ እኩል ተጠቃሚነትን ለማስፈን እና የትምህርት ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማገዝ ዩኒቨርሲቲው የድርሻውን እንደሚወጣም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ተጠቃሚነትና ውጤታማነት ለማሳደግ ብሎም ብቁ ተወዳዳሪ ለማድረግ በዩኒቨርሲቲው በሁሉም ካምፓሶች ያሉ የአገልግሎት መስጫ አካባቢዎችን ምቹና ሳቢ ማድረግ፣ ልዩ ድጋፎችን ማመቻቸትን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የተ/አገ/ማ/ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አየልኝ ጎታ ተናግረዋል ፡፡
በዕለቱ በማኅበራዊ ሣይንስና ሥነ-ሰብ ኮሌጅ የ2ኛ ዓመት የልዩ ፍላጎትና አካቶ ተማሪ ታደሰ እንግዳ ስለ አካል ጉዳተኝነት ጠቅለል ያለ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የሚደረግላቸውን ድጋፍ የየተመለከተ የዳሰሳ ጽሑፍ አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም የልዩ ፍላጎት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ አብዮት በላይነህ ለአካል ጉዳተኞች የተደረጉ ድጋፎችና ውስንነቶች ላይ ያተኮረ ሪፖርት አቅርበዋል፡፡
ተሳታፊዎች የቀረቡትን ጽሑፎች፣ የዩኒቨርሲቲውን ነባራዊ ሁኔታ እና የሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችን ተሞክሮ መነሻ በማድረግ በተለይም ከጥቅማ ጥቅም፣ ከመማሪያ ክፍሎች ምቹነት እና ከአመራሮች ተባባሪነት ጋር ተያይዞ ያሉ ውስንነቶች ላይ እንዲሁም እንደ አገር ለአካል ጉዳተኛ የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚሰጡ አገልግሎቶችና ሌሎች ተያያዥ እንቅስቃሴዎች ላይ በሰፊው ተወያይተዋል፡፡
በፕሮግራሙ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የኮሌጅ ዲኖች፣ የትምህርትና የሥራ ክፍል ኃላፊዎች፣ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል፡፡